አዲስ አበባ —
የኢትዮጵያ መንግሥት የተናጠል የተኩስ ማቆም ካወጀ በኋላ፤ ህወሃት ጦርነቱን ገፍቶ ተቆጣጥሯቸው በነበሩ፤ የሰሜንና ደቡብ ጎንደር ዞኖች ስርና በአፋር ክልል በሚገኙ ወረዳዎች በሚኖሩና ይኖሩ በነበሩ ሰላማዊ ዜጎች ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈፀሙን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስና ፍትህ ሚኒስቴር ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ በጋራ ያወጡት የመጀመሪያ ደረጃ የምርመራ ሪፖርት ግኝት አመለከተ።
በተጠቀሱት አካባቢዎች 482 ሰዎች መገደላቸውን፣ በ109 ሴቶች ላይ የአስገድዶ መደፈር መፈፀሙንና በ165 ሰዎች የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው ሪፖርቱ ይፋ አድርጓል።
ህወሃት በቀረበው ሪፖርት ላይ እስካሁን ቀጥተኛ ምላሽ አልሰጠም። ሆኖም ከዚህ ቀደም መሪዎቹ በተለያየ ጊዜ በሰጧቸው ምላሾች በሚቀርቡባቸው ውንጀላዎች ላይ ጉዳዩ ገለልተኛ የሆኑ ዓለም አቀፍ ተቋማት እንዲመረምሯቸው ከመጠየቅ ውጪ ክሶቹን አይቀበሏቸውም።