በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የኢትዮጵያ መንግሥት መቀሌ የሚገኘውን የመከላከያ ማሰልጠኛ ተቋም ዛሬ በአየር መምታቱን አስታወቀ


በመቀሌ ከተማ ዓዲ ሃቂ ገበያ አካባቢ
በመቀሌ ከተማ ዓዲ ሃቂ ገበያ አካባቢ

- በትናንቱ የአየር ጥቃት 15 ሰዎች መቁሰላቸውን የመቀሌ ነዋሪዎች ተናግረዋል

የኢትዮጵያ መንግሥት "አሸባሪ" የሚለው የታጠቀ ቡድን እንደሚጠቀምበት የገለፀውን መቀሌ የሚገኘውን የመከላከያ ማሰልጠኛ ተቋም ዛሬ በአየር መምታቱን አስታወቀ።

በሌላ በኩል ትናንት መቀሌ ከተማ ውስጥ እንደተፈፀመ በተገለፀ የአየር ድብደባ አሥራ አምስት ሰዎች መቁሰላቸውን በመቀሌ አይደር ሪፈራል ሆስፒታል ህክምና በመከታተል ላይ የሚገኙ ታካሚዎች ለቪኦኤ ተናግረዋል።

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ዛሬ ባወጣው መግለጫ “አሸባሪው ህወሃት” ሲል የጠራውና እራሱን “የትግራይ መንግሥት” እያለ የሚጠራው አካል “የትግራይን ህዝብ ከህፃን እስከ አዋቂ ለወረራ በማንቀሳቀስ በወሎ መርሳ አቅጣጫና በሃራ ጭፍራ በኩል አሰማርቷል” ብሏል።

መግለጫው አያይዞም የአማራና የአፋር ወጣቶች ከሠራዊቱ ጋር ተሰልፈው እንደ ክልል ልዩ ኃይሎችና ሚሊሽያ በግንባር እየተዋጉ መሆናቸውን ጠቁሞ የአየር ኃይሉም በግንባር መሥመሮችና በጥልቀት እየገባ “የመሳሪያ ማከማቻ፣ የጥገና ቦታዎችን፣ ማሰልጠኛዎችን፣ የማዘዣ ጣቢያዎችን እና ሎጂስቲክስ የሚያቀርቡና ሃብት የሚያሸሹ ተሽከርካሪዎች እንዲሁም ከባድ መሳሪያዎቻቸውን አውድሟል” ብሏል።

በሌላ በኩል የህወሃት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ በትዊተር ገፃቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት “የዐቢይ አህመድ አየር ኃይል ዛሬ ከሰዓት በኋላ መቀሌ የሚገኙ ቦታዎችን ዒላማ ያደረጉ ሦስት የማጥቃት ሙከራዎችን አድርጓል፤ እስካሁን የአየር መከላከያ ኃይላችን ህዝቡን መጠበቅ ችሏል፤ በዚህ መሀል ግን የተዳከመው የዐቢይ ሠራዊት በየቦታው ከፍተኛ ሽንፈት እያስተናገደ ነው” ብለዋል።

ማምሻውን ከአሜሪካ ድምፅ የተጠየቁት የመንግሥት ኮምዩኒኬሽንስ አገልግሎት ሚኒስትር ዶ/ር ለገሠ ቱሉ “ህወሃት ይጠቀምበታል” የተባሉትን የመከላከያ ማሰልጠኛ ተቋም በአየር መምታቱን ገልፀዋል።

“ቀድሞ የሰሜን እዝ ይዞታ የነበረና ለሰሜን እዝ ወታደራዊ ማሰልጠኛና ማዘጋጃ ሆኖ ያገለግል የነበረ ተቋም ነው። በኋላ ሰሜን እዝን በማትቃት አሸባሪው ቡድን እንደ እራሱ ማሰልጠኛ ወስዶ የራሱን ወታደሮች የሚያሰለጥንበትና የሚያዘጋጅበት ወታደራዊ የሥልጠና ቦታ ነው” ያሉት ዶ/ር ለገሠ ቱሉ ኢላማውን የፈፀመ ጥቃት ተፈፅሟል ብለዋል።

(ዝርዝር ዘገባውን ከተያያዘ የድምፅ ፋይል ያዳምጡ)

የኢትዮጵያ መንግሥት መቀሌ የሚገኘውን የመከላከያ ማሰልጠኛ ተቋም ዛሬ በአየር መምታቱን አስታወቀ
please wait

No media source currently available

0:00 0:06:36 0:00


XS
SM
MD
LG