በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በኢትዮጵያ ጉዳይ ከፍተኛ ውይይት ተደረገ


የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን
የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ቀውስ ላይ ከፍተኛ ስብሰባ ጠርተው አስተናግደዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ በተቀናጀውና ጉዳዩን በቅርብ ይከታተላል በተባለው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብሊንከንና የአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች ልዩ ልዑክ ጄፍሪ ፌልትማን በጋራ ባስተናገዱት ስብሰባ ላይ የአፍሪካ ኅብረት ከፍተኛ ተጠሪና የምሥራቅ አፍሪካው የጋራ ልማት ባለሥልጣን ኢጋድ ሊቀመንበር ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ፣ የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ፣ የአውሮፓ ኅብረት ከፍተኛ ተጠሪ ጆሴፕ ቦሬል፣ የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኤልዛቤጥ ትረስ፣ የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኒየልስ አላን እንዲሁም የፈረንሣይ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ፍሬድሪክ ክላቪየር ተገኝተዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብሊንከን ስብሰባውን ያስተናገዱት ከአፍሪካ ኅብረት ከፍተኛ ተጠሪ ኦባሳንጆ ጋር ከተወያዩ በኋላ መሆኑን የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ ቢሮ ማምሻውን ባወጣው መግለጫ አመክልቷል።

ለቀውሱ ሰላማዊ መፍትሔ ለማስገኘት በአፍሪካ ኅበረትና በኢጋድ መካከል የቅርብ ቅንጅት የመኖሩን ሃሳብ እንደሚደግፉ ተሰብሳቢዎቹ ባልሥልጣናት መግለፃቸውን የመሥሪያ ቤቱ መግለጫ ይናገራል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላምን ለማስፈንና የሃገሪቱን አንድነት ለማስጠበቅ ሁሉም ወገኖች የኃይልና የጥቃት አድራጎቶችን በአስቸኳይ እንዲያቋርጡ፣ ወደ ሰፋና አካታች ንግግር መግባት የሚያስችል መሠረት ለመጣል ተኩስ እንዲያቆሙ ዩናይትድ ስቴትስ፣ የአውሮፓ ኅብረት፣ ፈረንሣይ፣ ጀርመንና እንግሊዝ ማሳሰባቸውንም የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ የፕሬስ መግለጫ ጠቁሟል።

እንዲሁም በግጭቱ ውስጥ ያሉ ወገኖች ሁሉ ዓለም አቀፍ ሕግን እንዲያከብሩ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ እየተጎሳቆሉ ላሉ ሁሉ እርዳታ ያለገደብ እንዲደርስ እንዲደረግም ጥሪ ማስተላለፋቸው ተገልጿል።

XS
SM
MD
LG