ህወሃት ጦርነቱን እንዲያቆም፣ ከአፋርና ከአማራ አካባቢዎች እንዲወጣና እንዲደራደር ዩናይትድ ስቴትስ እንደምታሳስብ የዩናይትድ ስቴትስ ዓለምአቀፍ ልማት ኤጀንሲ ዋና አስተዳዳሪ አስታወቁ።
ፌደራሉ መንግሥት በሽብር የፈረጀው ህወሃት ታጣቂዎች ሰሞኑን አማራ ክልል ውስጥ በተካሄዱ ውጊያዎች ወደ 14 ሺህ የፌደራልና የአማራ ክልል ተዋጊ ኃይል ደምስሰናል” ሲሉ የመከላከያ ሠራዊቱ በበኩሉ በሰሜን ወሎ ግንባር ተሰልፎ የነበረውን የህወሃት ኃይል መምታቱንና አካባቢዎቹን መቆጣጠሩን አስታውቋል።
እራሳቸውን “የትግራይ መከላከያ ኃይል” ብለው የሚጠሩት ታጣቂዎች “ዘመቻ ንጋት” ሲሉ የጠሩትን ዘመቻ ለማስተጓጎል በሁለት አውድ የተሰለፈን ከፍተኛ የሆነ የኢትዮጵያን መከላከያ ሠራዊትና የአማራ ክልል ኃይሎችን ደመሰሰን ሲሉ ትናንት መግለጫ አውጥተዋል።
የመቀሌ ዘጋቢያችን ሙሉጌታ አፅብሃ ባደረሰን ዘገባ መሰረት “ውጊያው ከነሃሴ 13 እስከ ከትናንት በስተያ ነሃሴ 15/2013 ዓ.ም እኩለ ሌሊት ድረስ መካሄዱንና በደሴ በኩል ወልገጤና፣ ዳሸና እና ሃሙሲት የተሰማሩ 6 ክፍለጦር ሠራዊትና 11 ሺህ ልዩ ኃይል በቆረጣ ወደ ደብረ ታቦር ያቀና የህወሃት ተዋጊዎችን ለማጥቃት ሲሞክር መደምሰሱን” ታጣቂዎቹ ማዕከላዊ ዕዝ የሚሉት አካል ባወጣው መግለጫ ተናግሯል።
በተጨማሪም ይኸው መግለጫ “በወልዲያና መርሳ መሥመር ስሪንቃ በተሰኘ አካባቢ ሦስት ሺህ የሚሆኑ የሪፐብሊካን ኃይሎች እና አንድ ብርጌድ ኮማንዶ ኃይል ተደምስሷል፤ የቀረውም ተበትኗል” እንደሚል ሙሉጌታ ዘግቧል።
በሌላ በኩል ደግሞ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና የአማራ ክልል ልዩ ኃይል የሕወሃት ኃይሎችን በመደምሰስ ቦታዎቹን መቆጣጠራቸውን ያስታወቁ ሲሆን የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ነሃሴ 14 በፌስቡክ ገፁ ላይ ባወጣው መግለጫ በፃድቃን ገ/ትንሳይ የሚመራውን የህወሃት ኃይል በሰሜን ወሎ ግንባር ላይ መምታቱንና በጋሸና መቄት፣ ሙጃና በንፋስ መውጫ አካባቢዎችም ከባድ ትግል እያደረገ እንደሚገኝ አስታውቋል።
በተጨማሪም መግለጫው ከጋሸና እስከ ዋድላ እንዲሁም ላሊበላ መሥመር ላይ ያሉ “አሸባሪ” ሲሉ የጠሩን ኃይል መደምሰሳቸውን አስታውቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የዩናይትድ ስቴትስ ዓለምአቀፍ ልማት ኤጀንሲ /ዩ ኤስ ኤ አይ ዲ/ አስተዳዳሪ ሳማንታ ፓወር ዛሬ ባወጧቸው ትዊቶች
ኤጀንሲያቸው "በህወሃት ጥቃት ከቤታቸው ለመፈናቀል በተገደዱባቸው የአፋርና የአማራ አካባቢዎች በግጭቱ ለተጎዱ ከ136 ሺህ በላይ ሰዎች ምግብ ማድረስ መጀመሩን” አስታውቀዋል።
አስተዳዳሪዋ አያይዘውም “ህወሃት ጦርነቱን እንዲያቆም፣ ከአፋርና ከአማራ አካባቢዎች እንዲወጣና እንዲደራደር ዩናይትድ ስቴትስ ማሳሰቧን ትቀጥላለች። የህወሃት የጥቃት ዘመቻ የሚያደርገው ቢኖር ጦርነቱንና የኢትዮጵያን ህዝብ መከራ ማራዘም ብቻ ነው" ብለዋል።