ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ዴልታ የሚባለው የኮሮናቫይረስ ልውጥ ዝርያ ሥርጭት እየጨመረ መሄዱ አስቸጋሪ የስቃይ ወቅት ተደቅኖብናል ሲሉ ከፍተኛው የተላላፊ በሽታዎች አዋቂው ዶ/ር አነተኒ ፋውቺ ተናገሩ።
የፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የህክምና ጉዳዮች ከፍተኛ አመካሪው ዶ/ር ፋውቺ ትናንት በኤቢሲ ቴሌቭዥን ቀርበው በሰጡት ቃለ መጠይቅ "ሁኔታው እየከፋ ነው የሚሄደው” ብለው ለዚህም ምክንያቶቹ መከላከያውን አንከተብም ያሉት በሚሊዮኖች የተቆጠሩ ሰዎች ናቸው ብለዋል።
ባለፉት ሳምንታት በቫይረሱ የሚያዙት ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩን ተከትሎ ሳይከተቡ የቆዩ እንዳንድ ሰዎች ለመከተብ እያሰቡ መሆናቸው ተገልጿል።
ሆኖም አሁንም ብዙ ሚሊዮኖች የጤና ባለሥልጣናት ውትወታቸውን ቢቀጥሉም የተለያዩ ምክንያቶችን በመስጠት የፈለገውም ቢሆን አልከተብም እያሉ ናቸው።
አሜሪካውያን ክትባቱን እንዲወስዱ በየቀኑ እየተማጸኑ ያሉት ዶ/ር አንተኒ ፋውቺ
"ብትከተቡ ራሳችሁን ከከባድ ህመም እና ከሞት ትታደጋላችሁ። ቫይረሱ እንዲዛመት ዕድል የሚሰጡት ያልተከተቡት ሰዎች ናቸው" ብለዋል። ባለፉት ስድስት ሳምንታት በሀገሪቱ ካለፈው የካቲት ወር ወዲህ ባልታየ ቁጥር በየቀኑ 70000 አዲስ ተጋላጮች እየተመዘገቡ ሲሆን አንዳንድ የኮቪድ-19 ተከታታዮች በበኩላቸው በዚህ አሁን በገባው የአውሮፓውያን ነሃሴ ውስጥ ዴልታ ዝርያ በይበልጥ እየተዛመተ ሲሄድ በየቀኑ ከ140,000 እስከ 300,000 ሰዎች ሊያዙ እንደሚችሉ ተንብየዋል።