በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የማሊ የሽግግር ፕሬዚደንት ጥቃት ተሰነዘረባቸው


ፎቶ ፋይል
ፎቶ ፋይል

የማሊ የሽግግር ፕሬዚደንት አሲሚ ጎይታ ዛሬ ማክሰኞ ዋና ከተማዋ ባማኮ በሚገኘው ታላቁ መስጅድ ሁለት ወንዶች በጩቤ ጥቃት እንደሰነዘሩባቸው የፈረንሳይ የዜና ወኪል ዘገበ።

ጥቃቱ የደረሰው በመስጅዱ የኢድ አል አድሃ በዓል ጸሎት ሥነ ስርዓት ላይ ሲሆን ጋዜጠኞች እንዳሉት የሽግግር ፕሬዚደንቱ ወዲያውኑ ከመስጅዱ ተወስደዋል። በጥቃቱ ጉዳት ደርሶባቸው እንደሆን ግን አልተረጋገጠም።

የማሊ የኃይማኖታዊ ጉዳዮች ሚንስትር ማማዱ ኮኔ ለኤ.ኤፍ.ፒ በሰጡት ቃል " አንድ አጥቂ ፕሬዚደንቱን በጩቤ ሊወጋቸው ሲሞክር ተይዟል" ብለዋል።

የባማኮው ታላቁ መስጊድ ዋናው አስኪያጁ ላቱስ ቱሬ በበኩላቸው አጥቂው ፕሬዚደንቱን በጩቤ ሊወጋ ተንደርድሮ ሌላ ሰው ወጋ ማለታቸውን ዘገባው ጠቅሷል። ባለስልጣናቱ ያሉትን በነጻ ምንጭ በኩል ለዚህ ዘገባ ማረጋገጥ እንዳልቻለ የዜና ወኪሉ ጨመሮ ገልጿል።

ማሊ ከዘጠኝ ዓመታት በፊት በሀገርዋ የጀመረውን እና ከዚያ ወዲ ወደጎረቤቶቹዋ ወደኒዠር እና ቡርኪና ፋሶ የተስፋፋውን ጽንፈኛ እስላማዊ ዓመጽ ለማስቆም ስትጣጣር ቆይታለች። በብዙ ሽዎች የተቆጠሩ ወታደሮች እና ሲቪሎች ተገድለዋል ብዙ መቶ ሽህ ዜጎችም ከመኖርያቸው ተሰደዋል።

ግጭቱ በመዲናዋ ባማኮም ባለው የፖለቲካ አለመረጋጋት እየተንጸባረቀ ሲሆን ባለፈው ነሃሴ ኮሎኔል ጎይታ ተመራጩን ፕሬዚደንት ኢብራሂም ቡባካር ኬይታን ከስልጣን ያወረደውን መፈንቅለ መንግሥት መምራታቸው ይታወሳል።

ባለፈው ግንቦት ደግሞ ኮሎኔሉ ሃገሪቱን ወደሲቪላዊ አስተዳደር እንዲመልስ ሃላፊነት የተሰጠውን የሽግግር መንግሥት ገልብጠው የስግግር ፕሬዚደንት ሆነው ተሰይመዋል።

XS
SM
MD
LG