በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

“የኢትዮጵያን ህልውና ለማስጠበቅ የሚደረገውን ሃገራዊ ጥሪ በመቀበል አስፈላጊውን ድጋፍ እናደርጋለን” - የኦሮምያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት


የኦሮሚያ ክልል ኮምኒኬሽን ሀላፊ አቶ ጌታቸው ባልቻ
የኦሮሚያ ክልል ኮምኒኬሽን ሀላፊ አቶ ጌታቸው ባልቻ

“የኢትዮጵያን ህልውና ለማስጠበቅ የሚደረገውን ሀገራዊ ጥሪ በመቀበል አስፈላጊውን ድጋፍ እናደርጋለን” ሲል የኦሮምያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። ቃል አቀባዩ አቶ ጌታቸው ባልቻ ለአሜሪካ ድምፅ በሰጡት ቃል በሀገሪቱ የሰሜን አካባቢዎች “ህወሃት እያደረገ ነው” ያሉትን ውጊያም አውግዘዋል።

የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ባወጣው መግለጫ "ህወሃት ለ27 ዓመታት የአገሪቱን ብሔር ብሔረሰቦች ነጣጥሎ በማጋጨት ጥላቻን ሲዘራ ቆይቷል” ብሏል።

ዜጎችን ያለጥፋታቸው ስም እየሰጠ ሲያሰቃይ የነበረና በተለይ የኦሮሞን ሕዝብ ሴት ወንድ ሳይል ያሰቃየ እንደዚሁም አረመኔያዊ ድርጊቶችንም ሲፈፅም የኖረ ቡድን ነው” ሲል ወንጅሏል።


“መንግሥት የሀገሪቱን ዜጎች ለመጠበቅ ሲሠራ ቆይቶ ከስምንት ወራት በኋላ የተናጠል ትኩስ አቁም ውሳኔ አሳልፏል” ያሉት የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ባልቻ “የክልላቸው መንግሥት ማንኛውንም የሀገር ጥሪ ተቀብሎ ሰላምን ለማስፈን ዝግጁ ነው” ብለዋል።

“ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በሃገር አቀፍ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚደረግ ማንኛውም ዓይነት ትንኮሳና በውጭም የሚደረግ ማንኛውንም ወረራ የመከላከል ኃላፊነቱን ሲወጣ የነበረና ሃገርን ገንብቶ ያቆየ ሕዝብ ነው። ስለዚህ ይሄ ሕዝብ በሚፈለገው ደረጃ ተሳትፎውን እያደረገ እንዳለ ይታወቃል።” ካሉ በኋላ ይህንን ተሳትፎ አጠናክረው በቅንጅት እያከናወኑ መሆኑን ገልፀዋል።

አቶ ጌታቸው አክለውም “የኦሮምያ ክልል ሕዝብና መንግሥት ኢትዮጵያን በመገንባት ውስጥ የሚመጥነውን አስተዋፅዖ ሲያበረክት መቆየቱን አስታውሰው "የሀገርንና የህዝብን ሉዓላዊነትና ነፃነትን ለማስከበር በሚከፈለው መስዋዕትነት ላይም እራሱን ቆጥቦ አያውቅም” ብለዋል።

“በፌደራል መንግሥት የታወጀው የተናጠል ተኩስ አቁም አርሶ አደሩ በክረምት ወቅት ተረጋግቶ እንዲያርስ፣ ለዜጎች እርዳታ እንዲደርስና ግጭት እንዳይባባስ ቢሆንም ህወሓት ግን የተፈጠረበትን የጥፋት ስሜት መቆጣጠር አልቻለም” ብለዋል አቶ ጌታቸው።

ስለዚህ መንግሥት ሰላም ለማስፈን የሚያደርገውን ማንኛውንም ተግባር በመደገፍ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የክልሉን ህዝብ በማስተባበር የህወሃትን የክፋት ተግባር ለመመከት እየሠራ ነው” ብለዋል።

የኦሮምያ ክልል የሀገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ ባወጣው መግለጫ ላይ አስተያየታቸውን ለቪኦኤ የሰጡት የኦሮሞ ነፃነት ግንባር የፖለቲካ መኮንን አቶ ያሶ ከበበው “ሰላምን ለማስፈን ሁለቱም ወገኖች በጠረጴዛ ዙርያ መነጋገር አለባቸው” ብለዋል።

የህወሃት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ የትግራይ ግዛቶች ሙሉ በሙሉ እስኪመለሱ የክልሉ ኃይሎች የሚወስዱትን እርምጃ እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል። “የፌዴራል መንግሥት ኃይሎች ከዚህ በኋላ የትግራይ ሥጋት እንዳይሆኑ ለማድረግ የሚያስችል ሥራ መሥራታችንን እንቀጥላለን” ሲሉ ከቪኦኤ ጋር በሳተላይት ስልክ በነበራቸው ቆይታ ገልፀዋል።

XS
SM
MD
LG