በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

“የውጭና የውስጥ ጠላቶች ተናበው የከፈቱብንን ጥቃት መክተን እንቀለብሰዋለን“ ሲሉ ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ ገለጹ


ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ

“ለትግራይ ሕዝብ ያለንን ሐሳብ፤ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ያለንን ቦታ ለመጨረሻ ጊዜ አሳይተናል” ያሉት ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ “ለሕዝባችን ስንል የከፈልነው ዋጋ ባልገባቸው ደካሞች ምክንያት ውጤት አላመጣም“ ሲሉ ዛሬ በማህበራዊ ሚዲያ ገጾቻቸው ባሰፈሩት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጁንታው ያሉት ሕወሓት “የኢትዮጵያ ህልውና ቀንደኛ ጠላት መሆኑን ደግሞ እያስመሰከረ ነው፤ ይሄንንም “መላ ሕዝባችንን አስተባብረን እንቀለብሰዋለን“ ነው ያሉት።

የውጭና የውስጥ ጠላቶች ተናበው ጥቃት መክፈታቸውንም ጠቁመው፣ ሰብአዊ ርዳታ እንዲቀላጠፍ እየሠራን በሌላ በኩል ጥቃቱን መክተን እንቀለብሰዋለን ብለዋል።

ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብም “ስለ ርዳታና ስለ ረሐብ ሲናገር መቆየቱን ዘንግቶ፣ “የሰላም መንገድ ሊዋጥለት አልቻለም“ ያሉት ሕወሓት ሕጻናትን ሲያሰልፍ እንኳን ዝምታን መርጧል“ ሲሉ ተችተዋል። “እነዚህን ሁሉ ከግምት በማስገባት መንግሥት አስፈላጊውን ሁሉ ነገር በተገቢው መንገድ ያደርጋል“ም ብለዋል።

በሌላ በኩል መከላከያ ሰራዊት ትዕዛዝ በሚደርሰው ጊዜ አስፈላጊውን እርምጃ ሊወስድ በሚያስችል ቁመና ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡

ራሱን የትግራይ መከላከያ ኃይል በማለት የሚጠራው በሕወሓት የሚመራው ኃይል፣ አላማጣን እና ኮረምን መቆጣጠሩ ከተገለጸ በኋላ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለመጀመሪያ ጊዜ በጽሁፍ ባወጡት መግለጫ፣ ጁንታ ብለው የገለጹትን ሕወሓትን እና ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ተችተዋል፡፡

በማሕበራዊ ድረ ገጾቻቸው ባሰፈሩት መግለጫ “ለትግራይ ሕዝብ ያለንን ሐሳብ፤ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ያለንን ቦታ ለመጨረሻ ጊዜ አሳይተናል” በማለት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በሰብአዊነት ላይ የተመሠረተ የተናጠል የተኩስ አቁም መደረጉን አስታውሰዋል።

አክለውም “ሰላም የተወሰነ ዋጋ እንደሚያስከፍለን ብናውቅም ይህ ግን የመጨረሻ ሰላማዊ ዕድል ነው“ ካሉ በኋላ “የሰላም መንገድ ሊዋጥለት አልቻለም“ በማለትም ሕወሓትን ወንጅለዋል።

ሕወሓት ሕጻናትና ወጣቶችን በአደንዛዥ ዕጽ እያሳበደ ወደ ጦርነት እየማገደ ይገኛል“ ሲሉም የገለጹ ሲሆን “የመከላከያ ሠራዊቱ እነዚህን ሕጻናት ወታደሮች የመታደግ ሞራላዊ ግዴታ ወድቆበታል“ ብለዋል።

ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ “ለሕዝባችን ስንል የከፈልነው ዋጋ ባልገባቸው ደካሞች ምክንያት ውጤት አላመጣም“ ሲሉም በመግለጫቸው አንስተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ሕወሓት “የኢትዮጵያ ህልውና ቀንደኛ ጠላት መሆኑን ደግሞ እያስመሰከረ ነው፤ ይሄንንም መላ ሕዝባችንን አስተባብረን እንቀለብሰዋለንም ነው ያሉት።

የውጭና የውስጥ ጠላቶች ተናበው ጥቃት መክፈታቸውንም ጠቁመው፣ በአንድ በኩል ሰብአዊ ርዳታ እንዲቀላጠፍ እየሠራን በሌላ በኩል የውጭና የውስጥ ጠላቶች ተናበው የከፈቱብንን ጥቃት መክተን እንቀለብሰዋለን“ ብለዋል

ከሰብዓዊ እርዳታ ጋር በተያያዘ በእርሳቸው አገላለጽ “ጁንታው ዋሻ ውስጥ ገብቶ ሕዝቡ በረሐብ ሊያልቅ ነው እያለ ሲያላዝን“ የነበረ ሲሆን ለሕዝቡ ሲባል ሰብአዊ የተኩስ አቁም ሲደረግ ደግሞ “የረሐቡን አጀንዳ ትቶ የጦርነት ነጋሪት መጎሰም ጀመረ“ ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡

በዚህ ረገድ ዓለም አቀፉን ማሕበረሰብም “ስለ ርዳታና ስለ ረሐብ ሲናገር መቆየቱን ዘንግቶ ሕወሓት ሕጻናትን ሲያሰልፍ እንኳን ዝምታን መርጧል“ ሲሉ ተችተዋል። የርዳታ መግቢያ ኮሪደሮችን የግጭት ቦታዎች ሲያደርጋቸው የርዳታ ድርጅቶች አሁንም መንግሥትን ለመውቀስ እንደሚቃጣቸውም ነው ያነሱት። “እነዚህን ሁሉ ከግምት በማስገባት መንግሥት አስፈላጊውን ሁሉ ነገር በተገቢው መንገድ ያደርጋል“ ነው ያሉት።

ሕዝባችን ከሐሰተኛ መረጃዎች እና ከጠላት ፕሮፓጋንዳ ራሱን እንዲጠብቅ ሲሉ ያሳሰቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ “የውስጥና የውጭ ኃይሎች ፕሮፓጋንዳቸውን አቀናጅተው ሕዝብን ለመከፋፈል እየሠሩ ነው ሲሉም ነው“ የገለጹት። በመሆኑም ሕዝቡ እንደ ከዚህ በፊቱ ሁሉ እንደ አንድ ሠራዊት ሆኖ ለሀገሩ ህልውና በመቆም፣ የመከላከያ ሠራዊቱን በሁሉም ነገር በመደገፍ፣ የውጪውን ጫና እና የውስጡን ትንኮሳ እንዲመክትና እንዲቀለብስ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግሥት አስፈላጊውን ሁሉ ነገር በተገቢው መንገድ ያደርጋል“ ከማለት ውጭ ስለሚወሰደው እርምጃ በግልጽ ያሉት ነገር የለም፡፡

በሌላ በኩል መከላከያ ሰራዊት ትዕዛዝ በሚደርሰው ጊዜ አስፈላጊውን እርምጃ ሊወስድ በሚያስችል ቁመና ላይ እንደሚገኝ የመከላከያ ሰራዊት የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ገልጸዋል፡፡

ኮሎኔል ጌትነት የተኩስ አቁም እርምጃ በክላሽና በመድፍ ብቻ አይደለም፣ ከቃላት መወራወርም መቆጠብን ጭምር ያካተተ ነው ማለታቸውንም ነው ጋዜጣው ያስነበበው።

መቼና ምን ማድረግ እንዳለብንም ጠንቅቀን እንውቃለን ያሉት ኮሎኔል አዳነ፤ መከላከያ ሰራዊት ትዕዛዝ በሚደርሰው ጊዜ አስፈላጊውን እርምጃ ሊወስድ የሚችልበት አቋም ላይ እንዳለ አስታውቀዋል።

መንግስት የተናጥል ተኩስ አቁም ቢያውጅም፣ የሕወሓት ኃይሎች ራያን እና ሁመራን ጨምሮ ትንኮሳ ካደረገ ከባድ አጸፋዊ እርምጃ እንደሚወሰድበት የመከላከያ ሰራዊት ግንባታ ስራዎች ዋና አስተባባሪ ሌተናል ጄኔራል ባጫ ደበሌ ከሁለት ሳምንታት በፊት ገልጸው ነበር፡፡

ይሁን እንጂ የሕወሓት ኃይሎች በደቡብ ትግራይ በኩል በራይ ኮረምን እና አላማጣን ከመቆጣጠራቸው ባለፈ በምዕራብ ትግራይም ውጊያ ስለመኖሩ በመገለጽ ላይ ነው፡፡

ሕወሓት በአማራ ክልል ተወረዋል ያላቸውን የትግራይ ግዛቶች እስኪያስመልስ ውጊያውን እንደሚቀጥል በተደጋጋሚ የገለጸ ሲሆን፣ ኮረምን እና አላማጣንም በውጊያ ማስለቀቁን ነው ያስታወቀው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ በፌዴራል መንግስት በኩል የተባለ ነገር ባይኖርም፣ መንግሥት በአንድ ወገን የወሰደውን የተኩስ አቁም ውሳኔ እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም ሕወሓት መሰረተ ሰፊ የሆነ ወረራና ጥቃት ማድረግ ጀምሯል ያለው የአማራ ክልል መንግስት ከዛሬ ጀምሮ ከመከላከል ወደ ማጥቃት መሸጋገሩን በኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው ሙሉነህ በኩል አስታውቋል፡፡

(የአዲስ አበባውን ዘጋቢያችንን ኬኔዲ አባተ፣ የመቀሌው ዘጋቢያችን ሙሉጌታ አጽብሐና የባህርዷሯ ዘጋቢያችን አስቴር ምስጋናውን ያጠናቀሩትን ሁሉንም ያካተተ ዘገባ ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያዳምጡ)

please wait

No media source currently available

0:00 0:17:43 0:00XS
SM
MD
LG