በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኮረምና አላማጣን ማስመለሳቸውን አቶ ጌታቸው ረዳ ተናገሩ


ፎቶ ፋይል፡
ፎቶ ፋይል፡

- “በጀመርነው የሕልውና ትግል ተፈጥሯዊ እና ታሪካዊ መብታችንን እናረጋግጣለን” - የአማራ ክልል መንግሥት - “ተኩስ ወደማቆም ድርድር እንዲገቡ ጥሪያችንን በድጋሚ እናሰማለን” - የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት

“አሉላ ኣባ ነጋ” በሚል የሰየሙትን ዘመቻ ተከትሎ "የትግራይ እናቶች ዘመቻ" በሚል ኣዲስ ስያሜ በደቡብ እና ምዕራብ ትግራይ በጀመሩት አዲስ ዘመቻ ተወረዋል ያሏቸውን የትግራይ መሬቶች በማስመለስ ኮረም እና ኣላማጣ ከተሞች በቁጥጥሩ ስር ማስገባታቸውን የትግራይ ክልል ፕሬዝዳንት ኣማካሪ ኣቶ ጌታቸው ረዳ ገለፁ።

አቶ ጌታቸው በሳተላይት ስልክ ከአሜሪካ ድምፅ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳሉት " እየተካሄደ ያለውን ውግያ ሆን ብለው ከኣማራ ሕዝብ ጋር ለማስተሳሰር እየሞከሩ ያሉ ቡዱኖች የአማራ ሕዝብ ሴቶች እና ልጃገረዶች ከመድፈር ፣እናቶች ከመግደል ፣ የውጭ ወራሪ በማስገባትና ንብረት ከማዘረፍ ጋር የሚያያዝ ክብር የለውም " ብለዋል። በኣሁኑ ሰዓትም በደቡብ እና ምዕራብ ትግራይ ውጊያ የቀጠለ መሆኑንም ገልፀዋል።

በሌላ በኩል ሕወሓት ያለ የሌለ ኃይሉን ተጠቅሞ በክልላችን ላይ ወረራ ፈፅሟል ያለው የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በጀመርነው የሕልውና ትግል ተፈጥሯዊ እና ታሪካዊ መብታችንን እናረጋግጣለን ሲል ለሚመለከታቸው ሁሉ ጥሪ አቅርቧል። የአማራ ሕዝብ የማንነትና የወሰን ጥያቄ እያነሳ ሲታገልባቸው የቆዩትን ራያ፣ አላማጣና ኮረም አካባቢዎች ህወሓት በድጋሚ ወሯል በማለትም ነው የክልሉ መንግሥት በመግለጫው ላይ አስፍሯል::

“የኢትዮጵያ መንግሥት የወሰደውን የተናጥል የተኩስ አቁም ውሳኔ ተከትሎ ሕወሓት የሚያደርገውን እብሪተኛ እንቅስቃሴ መሰረት በማድረግ የማያዳግም እርምጃ እንዲወሰድ በአጽንዖት እናሳስባለን” ብሏል የክልሉ መንግሥት መግለጫው።

“የትግራይ መከላከያ ኃይሎች፣ የአማራ ክልል ኃይሎችና የኢትዮጵያ ብሄራዊ መከላከያ ኃይሎች በአካባቢው ላሉ ሲቪሎች ጥቅምና የኢትዮጵያን ሃገራዊ አንድነት ለመጠበቅ ሲሉ ተኩስ ወደማቆም ድርድር እንዲገቡ ጥሪያችንን በድጋሚ እናሰማለን” ሲል የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት አስታውቋል።

የመሥሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ ትናንት በሰጡት መግለጫ “በተደራጁ ወታደራዊም ይሁን የፀጥታ ኃይሎች ወይም በውንብድና አድራጎት ላይ በተሠማሩ ክፍሎች ትግራይ ክልል ውስጥ በሲቪሎች ላይ የሚፈፀሙ የበቀል ጥቃቶችን ሁሉ አጥብቀን እናወግዛለን” ብለዋል።

በተጨማሪም የሲቪሎች ደኅንነት መጠበቅን ጨምሮ የታጠቁ ወገኖች ሁሉ ዓለምአቀፍ የሰብዕና ህጎችን የሚጥሱና የሰብዓዊ መብቶች በደሎችን የሚፈፅሙ ሁሉ በተጠያቂነት እንዲያዙ ሃገራቸው እንደምታሳስብ አመልክተዋል።

ፕራይስ ቀጥለውም “በተደጋጋሚ እንዳልነው የኢትዮጵያን የውስጥ ወሰኖች በኃይል ለመለወጥ የሚደረግ ማንኛውም ጥረት ተቀባይነት የለውም” ብለዋል።

“ድንበርን የመሳሰሉ ማንኛውም እንዲህ ዓይነት ብሄራዊ ትርጉም ያለው ጉዳይ መወሰን ያለበት በኢትዮጵያ ህዝብ የመግባባት ንግግር እንጂ በጠብመንጃ አፈሙዝ ሊሆን አይገባውም” ብለዋል ፕራይስ።

በሌላ ዜና ራሱን የትግራይ ኃይል ብሎ የሚጠራው አካል አላማጣንና ኮረምን በመቆጣጠሩ አካባቢውን በስጋት ለቀው ወደ ሰሜን ወሎ የዘለቁ ተፈናቃዮች ገለጹ፡፡

በዐስር ሺዎች የሚገመቱ የአላማጣ፤ ዋጃና ጥሙጋ አካባቢ ኗሪዎች ወደቆቦና ወልዲያ ከተሞች መሸሻቸውንም ገልፀዋል።

(ዘገባው ያጠናቀሩት ሳራ ፍሰሃየ ፣ አስቴር ምስጋናውና መስፍን አራጌ ናቸው ሙሉ ዘገባውን ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያዳምጡ)

ኮረምና አላማጣን ማስመለሳቸውን አቶ ጌታቸው ረዳ ተናገሩ
please wait

No media source currently available

0:00 0:15:08 0:00


XS
SM
MD
LG