በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

"ቫይረሱ እንደሰደድ እሳት እንዲዛመት ከተፈቀደ ብዙ ሚሊዮኖች አደጋ ላይ መውደቃቸው አይቀርም" - አንቶኒዮ ጉተሬዥ


የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸኃፊ አንቶንዮ ጉቴሬዥ
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸኃፊ አንቶንዮ ጉቴሬዥ

በዓለም ዙሪያ በኮቪድ - 19 ምክንያት ሕይወታቸውን ያጡት ሰዎች ቁጥር ከአራት ሚሊዮን ማለፉን ተከትሎ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸኃፊ አንቶንዮ ጉቴሬዥ "ይሄ ቫይረስ እንደሰደድ እሳት እንዲዛመት ከተፈቀደ አሁንም ብዙ ሚሊዮኖች አደጋ ላይ መውደቃቸው አይቀርም" ሲሉአስጠንቅቀዋል።

ጉቴሬዥ በጹሑፍ ባወጡት መግለጫ የኮቪድ - 19 ክትባት በእጅግ ሃብታሞቹ እና እጅግ ደሃዎቹ ሃገሮች መካከል በፍትሃዊነት እየተዳረሰ አይደለም ከዚያም ሌላ ዴልታ የተባለው እና በይበልጥ ተላላፊው የቫይረሱ ዝርያ በከፍተኛ ፍጥነት እየተዛመተ ነው

ስለሆነም አብዛኛው የዓለም ክፍል አሁንም አደጋ እንደተደቀነበት ነው በማለት አስጠንቅቀዋል። የኮቪድ አስራ ዘጠኝ ክትባቱ ምርቱ ቢያንስ በዕጥፍ እንዲያድግ እና በኮቫክስ በኩል ፍትሃዊ በሆነ መንገድ እንዲዳረስ ለማድረግ የሚሠራ ክትባቱን የሚያመርቱ ሃገሮች፥ የዓለም የጤና ድርጅት እና ዓለምአቀፍ የገንዘብ ተቋማት ያቀፈ የአስቸኳይ ጊዜ ግብረ ኃይል እንዲቋቋም ዋና ጸሐፊው ሐሳብ አቅርበዋል።

ዋና ጸኃፊው ጉቴሬዥ አስከትለው፤ "የዘመናችን አጣዳፊ የሞራል ፈተና የዚህ ክትባት በፍትሃዊነት መዳረስ ነው ፥ ሁሉም ሰው እስካልተከተበ ድረስ ደግሞ አንድም ሰው ከቫይረሱ አደጋ ነጻ ሊሆን አይችልም " ብለዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ የጃንስ ሃፕኪንስ ዩኒቨርስቲ የኮቪድ አስራ ዘጠኝ መረጃ ማዕከል ባወጣው አሃዝ መሰረት በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው ከተረጋገጠው 185 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሰዎች መካከል 4 ሚሊዮን 2 ሽህ 909 ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል።

የዓለም የጤና ድርጅትም በበኩሉ በፍጥነት የሚተላለፈው የዴልታው ዝርያ አደጋ በተደቀነበት ባሁኑ ወቅት አገሮች የእንቅስቃሴ ክልከላዎችን እና ሌሎችንም ገደቦች በሙሉ ሲሰርዙም ሆነ ሲያላሉ እጅግ ከፍተኛ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስቧል።

የድርጅቱ የአጣዳፊ ሁኔታዎች መርሃ ግብር ሃላፊው ዶክተር ማይክ ራያን ትናንት ጄኔቫ ላይ ለጋዜጠኞች በሰጡት ቃል "ብዙ ሰዎች ስለተከተቡ የቫይረሱ ስርጭት አይባባስም የሚለው አመለካከት የተሳሳተ እንደሆነ ገልጸዋል፥ በማንኛውም የዓለም አካባቢ ቢሆን ሁሉ ሰው ተከትቧል፥ ሁሉ ነገርወደቀደመው ሁኔታ ተመልሷል ማለት እጅግ አደገኛ ነው" ሲሉ አሳስበዋል ።

XS
SM
MD
LG