በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ብሊንከን ስለኢትዮጵያ ምርጫ የሰጡት መግለጫ


የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን
የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን

ዲሞክራሲ የሚያብበው የአስተዳደር ተቋማት አሳታፊ፣ ግልጽነት እና ተጠያቂነት ያላቸው ህዝባቸውን የሚሰሙ ሲሆኑ ነው ያሉት የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን፣ ያ ጊዜ የማይሽረው ዕውነታ መሆኑን እያሰብን፣ በሰኔ አስራ አራቱ የኢትዮጵያ ብሂራዊ ምርጫ የመምረጥ መብታቸውን የተጠቀሙ ኢትዮጵያውያንን እናደንቃለን ሲሉ ተናገሩ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዛሬ ባወጡት መግለጫቸው ምርጫ መካሄዱ ብቻውን በቂ የዲሞክራሲም ሆነ የእውነተኛ ፖለቲካዊ ለውጥ መለያ ምልክት አይደለም ብለዋል።

የሰኔ አስራ አራቱ ምርጫ የተካሄደው ዘውግን መሰረት ያደረጉና የማኅበረሰቦች የእርስ በርስ ግጭትን ጨምሮ ሀገሪቱ በከባድ አለመረጋጋት ውስጥ ባለችበት እና የምርጫው ሂደት ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ነጻና ፍትሃዊ ባልሆነበት ሁኔታ ነው ብለዋል።

ተቃዋሚ ፓርቲዎች በምርጫው ላለመሳተፍ በወሰኑበት፥ ድምጻቸውን አጉልተው የሚያሰሙ የፖለቲካ መሪዎች በታሰሩበት፣ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ግጭት በቀጠለበት ድባብ ነው ብለዋል። ይህም የሃገሪቱን ሉዓላዊነት የሚያስጠብቅም፣ አንድነቷን የሚያረጋጋጥ እና ህገ መንግሥታዊ ስርዓትን የሚያጠናክር አስተዳደር ለመገንባት የሚያስችል ሁሉን አቀፍ ብሄራዊ ብሄራዊ መግባባት ለመፍጠር ጥረት መደረግ እንዳለበት የሚያሰምር ነው ብለዋል።

በዚህ የድህረ ምርጫ ወቅት ኢትዮጵያውያን እየተባባሰ የመጣውን ክፍፍል በአንድነት መጋፈጣቸው ወሳኝነት ይኖረዋል ያሉት የዩናይትድ ስቴትሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የፖለቲካ እና የማኅበረሰብ መሪዎች ሁከትን እንዳይቀበሉ ሌሎችን ወደግጭት የሚያነሳሱ ድርጊቶች እንዲቆጠቡ እናሳስባለን ብለዋል።

ዩናይትድ ስቴትስ ድህረ ምርጫ ውይይቶች፣ የግጭቶችን በመፍታት እና ብሄራዊ ዕርቅ ለማምጣት ኢትዮጵያዊያንን ለመርዳት ዝግጁ ነች ያሉት ሚኒስትር ብሊንከን ትግራይ ውስጥ ያለው ግጭት፣ ሁከት እና ያንዣበበው የጠና ረሃብ፣ ተኩስ ማቆምን፣ የኤርትራ ወታደሮች መውጣትን ጨመሮ አስቸኳይ እርምጃ የሚጠይቅ ነው ብለዋል። ተፈጽመዋል በተባሉ የጭካኔ አድራጎቶች ግልጽ ምርመራ እና እርዳታ ለሚፈልገው ህዝብ ያልተገደበ ተደራሽነት አስፈላጊ መሆኑም አክለው ዩናይትድ ስቴትስ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር በአላው አጋርነት ለመቀጠል እና ሁሉን አቀፍ የፖለቲካ ተሳትፎ በማድረግ ወደዲሞክራሲና ብሄራዊ አንድነት እንድትራመድ በሚደረጉ ጥረቶች ለማገዝ ዝግጁ ነች ብለዋል።

XS
SM
MD
LG