የሶማሌላንድ ፕሬዝዳንት ሙሳ ቢሂ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ልዑካን እና የዲፒ ወርልድ ዳይሬክተር ሱልጣን ቢን ሱለይማን በተገኙበት የበርበራ ወደብ የመጀመሪያ ዙር ማስፋፊያ ፕሮጀክት ተመርቆ በይፋ ሥራ መጀመሩን የኢዮጵያ የዜና አገልግሎት ዘግቧል።
በዲፒ ወርልድ 51%፣ በሶማሊላንድ 30% እና በኢትዮጵያ 19% ድርሳ የተያዘው የበርበራ ወደብ የመጀመሪያ ዙር ማስፋፊያ ፕሮጀክት 500 ሺህ ኮንቴነሮችን መያዝ የሚችል ተርሚናል እንደሆነና በአመት አንድ ሚልዮን ኮንቴነሮችን ማስተናገድ የሚችል መሆኑ ታውቋል።
ወደቡ ከዛሬ ጀምሮ ግዙፍ መርከቦችን በማስተናገድ ለቀጠናው በተለይ ለኢትዮጵያ ትልቅ ጥቅም እንዳለው ተገልጿል።
የኢትዮጵያ የትራንስፖርት ሚኒስትር ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ በሥነ ስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር የኢትዮጵያ ወጪና ገቢ እንቅስቃሴ ለማሳደግ ወደቦችን ማልማትና መጠቀም አስፈላጊ በመሆኑ የበርበራ ወደብ መከፈት ለኢኮኖሚው ትልቅ ሚና አለው ብለዋል።
የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴም በበኩላቸው እንደገለፁት የበርበራ ወደብ የመጀመሪያው ዙር ተርሚናል ሥራ መጀመር በቀጠናው የኢኮኖሚ ውህደት እንደሚያሳድግ አመልክተዋል።
የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ ሙሁመድ በበኩላቸው የሶማሌላንድ ልማትና እድገት ለኢትዮጵያ በተለይ ለሶማሊ ክልል እድገት ፋይዳው የጎላ መሆኑን እስገንዝበዋል።