በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ከኮቪድ-19 ክትባት ጋር የተያያዘ የልብ ጤና እክል ሊያጋጥም ይችላል - ሲዲሲ


ኮቪድ-19ን ለመከላከል ከሚሰጡት ክትባቶች መካከል ሁለቱን የወሰዱ ወንዶች ልጆች እና ወጣት ወንዶች ላይ ያልተለመደ የሆነ የልብ ህመም ሊያጋጥም እንደሚችል የዩናይትድ ስቴትስ የበሽታ መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል /ሲዲሲ/ አመለከተ።

የፌዴራል መንግሥት የጤና ማዕከል ትናንት ባወጣው መግለጫ እንዳለው የፋይዘር እና የሞደርና የኮቪድ ክትባቶችን የተከተቡ ከ1200 በላይ ሰዎች ማዮካርዳይቲስ የሚባለው የልብ ልባስ ጡንቻ መቆጣት እንዳጋጠማቸው አስታውቋል። ህመሙ ከሴቶች ይበልጥ ወንዶች ላይ በብዛት እንደተከሰተ እና በሁለት ጊዜ የሚሰጡት እነዚህን ክትባቶች የመጀመሪያውን እንደወሰዱ ሳይሆን ብዙውን ጊዜ ህመሙ የተፈጠረው ሁለተኛውን ከተወጉ በኋላ መሆኑን አብራርቷል።

ይህ የክትባቶቹ የጎንዮሽ ጉዳት የሚያስከትለው የህመም ምልክት ድካም እና የደረት ላይ ህመም መሆኑን አክሎ ያስረዳ ሲሆን የልብ ህመም መሆኑ በምርመራ የታወቀላቸው ሰዎች እጅግ አብዛኞቹ ሙሉ በሙሉ ማገገማቸውን ገልጿል።

ሲዲሲ አስከትሎም ከሁለቱ የኮቪድ ክትባቶች ጋር የተቆራኘ የልብ እክል ሊያጋጥም የሚችል ቢሆንም ክትባቱን መከተቡ የሚሰጠው ጥቅም እንደሚያመዝን ሳያሳስብ አላለፈም።

በሌላ ዜና ዋይት ሃውስ ለብራዚል በአንድ መርፌ የሚሰጠውን የጆንሰን ኤንድ ጆንሰንን ሦስት ሚሊዮን ክትባቶች ዛሬ መላኩን አስታወቀ።

ለብራዚል የተላኩት ክትባቶች የባይደን አስተዳደር በዚህ የአውሮፓ ሰኔ ወር ውስጥ ሰማኒያ ሚሊዮን ክትባቶችን ለሌሎች ሃገሮች ለመላክ በገባው ቃል መሰረት መሆኑ ተገልጿል።

በኮቪድ-19 የተነሳ 602,837 ሰዎች የሞቱባትን ዩናይትድ ስቴትስን በአሃዙ ብዛት በሁለተኝነት በምትከተላት ብራዚል ቁጥሩ 507,109 መግባቱን የጃንስ ሃፕኪንስ ዩኒቨርስቲ የኮቪድ መረጃ ማዕከል ሰንጠረዥ ያሳያል።

XS
SM
MD
LG