በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የአሜሪካ መንግስት ለልዩ ፍላጎት ትምህርት ብቻ በየዓመቱ 13 ቢሊዮን ዶላር ያወጣል - ወይዘሮ አዜብ አታሮ


ወይዘሮ አዜብ አታሮ - የልዩ ፍላጎት ትምህርት ባለሙያና አማካሪ
ወይዘሮ አዜብ አታሮ - የልዩ ፍላጎት ትምህርት ባለሙያና አማካሪ

በአሜሪካን አገር ልዩ ፍላጎት ያላቸውን ልጆች የሚያስተምሩ አካታች ትምህርት ቤቶች በስፋት ቢኖሩም ኢትዮጵያዊ ወላጆች በሚኖራቸው የግንዛቤ እጥረት ወይም የቅርብ ክትትል ማነስ ምክንያት ልዩ ፍላጎት ያላቸው ልጆቻቸው የሚገባቸውን ድጋፍ ላያገኙ እንደሚችሉ በልዩ ፍላጎት ትምህርት ዙሪያ የሚሰሩ ባለሙያዎች ይገልፃሉ። እነዚህ ወላጆች ለልጆቻቸው ስኬት ምን ማድረግ አለባቸው፣ ከትምህርት ቤቶችስ ምን አይነት ድጋፍ ይጠበቃል?

የአሜሪካ መንግስት ለልዩ ፍላጎት ትምህርት ብቻ በየአመቱ 13 ቢሊዮን ዶላር ያወጣል - ወይዘሮ አዜብ አታሮ
please wait

No media source currently available

0:00 0:07:26 0:00

(ዝርዝሩን ከላይ ከተያያዘው ፋይል ያዳምጡ)

ቀደም ባለ ዘገባችን ኢትዮጵያ ውስጥ ልዩ ፍላጎት ያላቸው ልጆች ተገቢውን ትምህርት የሚያገኙበት አካታች ትምህርት ቤቶች ባለመኖራቸው እንዲሁም በወላጆቻቸውና በማህበረሰቡ የእውቀት ማነስ ምክንያት መሆኑን ከዛ ጋር ተያይዞም የሚያጋጥሟቸውን ተግዳሮቶች ወላጆችና ባለሙያዎችን አነጋግረን አቅርበን ነበር።

በዚህ ጉዳይ ላይ ያናገርናት ወላጅ እናት አልማዝ ጥላሁን፣ የኦቲዝም ተጠቂ የሆነው የ16 አመት ልጇን የምትልክበት ትምህርት ቤት በማጣቷ እየደረሰባት ያለውን ችግርና ተስፋ መቁረጥ አካፍላን ነበር።

ልዩ ፍላጎት ያላቸው ልጆች ትምህርታቸውን ለመከታተል የሰለጠነ ባለሙያ፣ ለነሱ ተብሎ የተዘጋጀ የማስተማሪያ ቁሳቁስ እና የተለየ የመማር ማስተማር ሂደት ይፈልጋሉ።

በዛሬው ዝግጅታችን ታዲያ እነዚህ መሰረታዊ ፍላጎቶች ተሟልተው በሚገኙበት አሜሪካን አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊ ወላጆች በሚሰጡት አገልግሎቶች ምን ያክል ተጠቃሚ ሆነዋል? በጉዳዩ ላይ ያላቸው ግንዛቤስ ምን ያክል ነው ስንል በሜሪላንድ ክፍለ ግዛት የልዩ ፍላጎት ትምህርት ባለሙያና አማካሪ የሆኑትን ወይዘሮ አዜብ አታሮን ጠይቀናቸዋል።

በአሜሪካን አገር ልዩ ፍላጎት ኖሯቸው የሚወለዱ ህፃናት ከአንድ አመት ከስድስት ወራቸው ጀምሮ ልዩ ክትትል ማግኘት ይጀምራሉ። ሁሉም የመንግስት ትምህርት ቤቶች አካታች በመሆናቸውም ወላጆች ትምህርት ቤት ችግር አይገጥማቸውም። የአሜሪካ መንግስት ለልዩ ፍላጎት ትምህርት ብቻ በየዓመቱ 13 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያወጣም ወይዘሮ አዜብ ያስረዳሉ።

ልዩ ፍላጎት ባላቸው ልጆች የትምህርት አሰጣጥና ድጋፍ ዙሪያ ትልቁ ስህተት ሁሉንም በአንድ አይነት መልኩ ለመርዳት መሞከር ነው። መሆኑን ወይዘሮ አዜብ ያስረዳሉ።

ሌላው በአሜሪካን አገር የሚኖሩ ወላጆች ዘንድ የሚታየው ችግር ልዩ ፍላጎት ያላቸው ልጆቻቸውን ትምህርት ቤት ከላኩ በኃላ ክትትል ያለማድረግ ነው። ወይዘሮ አዜብ በቂ ትምህርት ቤቶችና እገዛ ባለበት አሜሪካን አገርም ቢሆን የልጆቻቸውን ጉዳይ ለትምህርት ቤቱ ወይም ለአስተማሪው ብቻ መተው ስኬታማ እንደማያደርግ ያሰምሩበታል።

ማንኛውም የሰው ልጅ በትክክለኛ መንገድ ትምህርትና ድጋፍ ካገኘ ሊሻሻልና ስኬት ላይ ሊደርስ ይችላል የሚሉት ወይዘሮ አዜብ በተለይ የተሟላ አገልግሎት ባሉባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ወላጆች ልዩ ፍላጎት ያላቸውን ልጆቻቸውን ከህፃንነት እድሜያቸው አንስቶ ተገቢውን ድጋፍና አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግና በቤት ውስጥም በቂ ክትትል በማድረግ ልጆቻቸውን ለራሳቸው ብቻ ሳይሆን ለቤተሰባቸውና ለማህበረሰቡ የሚጠቅሙ ልጆች ማፍራት ይቻላሉ ስሉ ምክራቸውን ለግሰዋል።

XS
SM
MD
LG