ዋሺንግተን ዲሲ —
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን አስተዳደራቸው ለዘጠና ሁለት ባለ ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ሃገሮች አምስት መቶ ሚሊዮን ብልቃጥ ክትባቶችን የምትለግስ መሆኑን ዛሬ ይፋ ያደርጋሉ፡፡
ዋሽንግተን ፕሬዚዳንቱ ዛሬ ይፋ የሚያደርጉት ልገሳ ክትባቱን ሰብስባ እያከማቸች ነው ከሚለው ወቀሳ ይገላግለኛል ብላ ተስፋ አድርጋለች፡፡
የፕሬዚዳንት ባይደን አስተዳደር የኮቪድ-19 ክትባት ድጋፍ ክትባቱ ለዓለም ህዝብ ሁሉ እንዲዳረስ ዲሞክራሲያዊ ሃገሮች በተቀናጀ መንገድ ለሚያደርጉት ጥረት መሰረት እንደሚጥል አመልክቷል፡፡
ዩናይትድ ስቴትስ ክትባቶቹን የምትልከው ክትባቱን ለችግረኞች ሃገሮች ለማዳረስ በተቋቋመው መርሃ ግብር በኮቫክስ አማካይነት ሲሆን ካሁን ቀደም ቃል የገባችው ሰማኒያ ሚሊዮን ክትባት በዚሁ በያዝነው ሰኔ ወር ውስጥ እንደሚደርስ ተገልጿል። ከዚያም ሌላ ካሁን ቀደም ለኮቫክስ መርሃ ግብር ሁለት ቢሊዮን ዶላር እንደለገሰች ይታወሳል፡፡
ዩናይትድ ስልቴትስ ቀደም ሲል ያቀደችው ተጨማሪ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ልትሰጥ የነበረ ሲሆን አሁን ግን ገንዘቡን አምስት መቶ ሚሊዮኑን ክትባት ለመግዛት ለሚያስፈልጋት የሦስት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዶላር ክፍያ ልታውለው ማቀዷ ታውቋል፡፡