በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የዩናይትድ ስቴትስ የኮንግረስ አባላት በኢትዮጵያ ጉዳይ


የዩናይትድ ስቴትስ የተወካዮች ምክር ቤት አራት አባላት ኢትዮጵያ ውስጥ ቀጥሏል ያሉትን ጦርነትና ሰብዓዊ ጉዳት የሚያወግዝ መግለጫ ከትናንት በስተያ አውጥተዋል።

“ሚሊዮኖች ለረሃብ ተጋልጠዋል፣ ለመፈናቀል ተዳርገዋል” ይላል የኮንግረስ አባላቱ የጋራ መግለጫ።

የኢትዮጵያ መንግሥት ግን “የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አቋም የተዛቡ መረጃዎችን ያለምንም ማጣራት ከመጋራትና ከማጋራት የመነጨ ነው” ይላል።

ግሪጎሪ ሚክስ፣ ማይክል ማካውል፣ ካረን ባስና ክሪስቶፎር ስሚዝን የመሳሰሉ የአሜሪካ ኮንግረስ አባለት ከሁለት ቀናት በፊት በጋራ ባስተላለፉት አቋም በትግራይ ቀጥሏል ያሉትን ጦርነትና ውድመት፣ በመላ አገሪቱ እየተባባሰ መጠቷል ሲሉ የገለጹትን የሰብአዊ መብት ጥሰት በጽኑ አውግዘዋል፡፡

በትግራይ በተከሰተው ጦርነት የአካባቢው ኗሪ ክፉኛ መጎዳቱን የጠቆመው መግለጫው ከአንድ ሚሊዮን የሚልቁ ሰዎች ተፈናቅለዋል፣ ከአምስት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑትን ደግሞ ወደ ከፋ ረሃብ እያሸጋገራቸው ነው ብሏል። ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጠረው ሁኔታ የሰፊውን የአፍሪካ ቀንድ ሰላምም እያናጋ ነው ይላል መግለጫው።

“ቀጥሏል” ያለውን ግጭትም “ተቀባይነት የሌለው” ሲል ነበር የገለጸው። ለሰብዓዊ ተራድኦ ሰራተኞች ደኅንነቱ የተጠበቀና አጋጅነት የሌለበት ተደራሽነትን በማመቻቸት ለጉዳት ተጋላጭ ለሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች አስቸኳይ እርዳታ እንዲቀርብላቸው ተጠይቋል።

የኮንግረስ አባላቱ ጦርነት ውስጥ የገቡት ወገኖች በፍጥነት ግጭት አቁመው በቅን መንፈስ የታጀበ ፖለቲካዊ ውይይት እንዲያደርጉም ጥሪ አስተላልፈዋል።

የኢትየጵያና የኤርትራ መንግሥታትም የኤርትራ ሰራዊትን ከኢትዮጵያ ሙሉ በሙሉ ለማስወጣት የገቡትን ቃል በፍጥነት ተግባራዊ ማድረግ አለባቸው ሲል ጥሪ አስተላልፏል መግለጫው።

የተባባሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ቢሮም ሆነ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በትግራይ የተፈጠረውን የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ጉዳት የመመረመር ሙሉ ሥልጣናቸው ዕውን እንዲሆንና ተደራሽነት እንዲያገኙም አሳስቧል።

ዝርዝሩን ከተያያዘው የድምጽ ፋይል ያድምጡ፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ የኮንግረስ አባላት በኢትዮጵያ ጉዳይ
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:11 0:00


XS
SM
MD
LG