በዩናይትድ ስቴትስ የህግ መወሰኛ ምክር ቤት የቨርሞንት ክፍለ ሃገር ሴኔተር ፓትሪክ ሌሂ በመግለጫቸው መግቢያ
"እአአ በ1984 በኢትዮጵያ በተራዘመ ድርቅ ሳቢያ በስፋት በተከሰተው የምግብ እጥረት እና በመንግሥት አድላዊ ፖሊሲዎች የተነሳ የደረሰውን ከባድ ረሃብ በዚያም ምክንያት ብዙዎቹ የትግራይ ተወላጆች የሆኑ ሰውነታቸው በረሃብ ያለቀ አንድ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን የተሰደዱበትን የሚዘገንን ቸነፈር በደንብ አስታውሰዋለሁ" ብለዋል።
ቆይቶ ዝናብ መጣል ጀመረ። ስደተኞቹም ወደቀያቸው ተመለሱ። ይሁን እንጂ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ሃገሪቱ በየጊዜው ግጭት እና የበቂ ምግብ ዕጦት ተለይቷት አያውቅም ሲሉም የዩናይትድ ስቴትሱ የህግ መወሰኛ ምክር ቤት አባል አክለዋል።
ዛሬ የትግራይ ህዝብ ዘግናኝ በሆነ ደረጃ ጭካኔ የተመላበት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ጥቃት እየተፈጸመበት ነው ያሉት ሴኔተር ሌሂ ህዝቡ በአጣዳፊነት የሚያስፈልገው የምግብ እርዳታ እንዳይደርሰው የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ወታደራዊ ኃይሎች እንዲሁም ሌሎች ታጣቂ ቡድኖች እየከለከሉ ናቸው" ብለዋል።
“ዩናይትድ ስቴትስ እና ሌሎችም ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ያደረጉ ቢሆንም የግጭቱ ተሳታፊ ወገኖች ግጭቱን አቁመው ሰላማዊ መፍትሄ ለመፈለግ የወሰዱት አንዳችም ትርጉም ያለው እርምጃ የለም" ሲሉ አክለዋል።
"ትግራይ ውስጥ የሚፈጸሙትን ግድያዎች፣ በግዴታ ከቀዬ ማፈናቀል፣ ወሲባዊ ጥቃቶች እና ሌሎችም የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንዲሁም በውሃ አቅርቦት ስፍራዎች እና በሆስፒታሎች እና በመሰል የጤና ማዕከሎች ላይ የሚደርሰውን ውድመት የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት አውግዟል።
የኢትዮጵያ መንግሥት እነዚህን ወንጀሎች የፈጸሙትን ተጠያቂ እንዲያደርግ የሲቪሎችን ደህንነት እንዲጠብቅ የሰብዓዊ ረድዔት ተደራሽነትን እንዲያረጋግጥ የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ጥሪ አቅርቦለታል በማለት አክለው የኤርትራም መንግሥት በገባው ቃል መሰረት ወታደሮቹ ወደግዛቱ መመለስ ነበረበት ብለዋል።
በአሁኑ ጊዜ ትግራይ ውስጥ የሚታየው አሳዛኝ ዕውነታ የረሃብ፣ በሰብዓዊ ፍጡር ላይ የሚፈጸም ወንጀሎች እና የዘር ማጥፋት አድራጎት ነው ሲሉ የቀጠሉት ሴኒተር ፓትሪክ ሌሂ ይህ እየደረሰ ያለውም በአንድ ምክንያት ነው፤ እሱም የአዲስ አበባና የአስመራ መንግሥታት በመመሳጠራቸው ነው። በሪፖርቶች መሰረት ትግራይ ውስጥ ያለው ሁኔታ ከዳርፉር የባሰ ሊሆን ይችላል ሲሉም አክለዋል።
አስከትለውም ትግራይ ውስጥ የሚፈጸመው የግፍ አድራጎት እንዲገታ፥ የምግብ እና ሌላም እርዳታ ተደራሽነት እንዳይከለከል ለግጭቱ ሰላማዊ መፍትሄ እንዲፈለግ እና የጭካኔ አድራጎት ሰለባ የሆኑት ዜጎች ፍትህ እንዲያገኙ እጠይቃለሁ ብለዋል።