በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ቦርኪና ፋሶ ውስጥ ሰዎች መገደላቸውን ተከትሎ የሃዘን ጊዜ ታወጀ


ቦርኪና ፋሶ ሰሜናዊ ክፍለ ሀገር ውስጥ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በተፈጸመ ጥቃት አንድ መቶ ስድሳ ሰዎች መገደላቸውን ተከትሎ የሀገሪቱ መንግሥት የሶስት ቀን የሃዘን ጊዜ አውጇል።

ዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል የሀገር ውስጥ ሆስፒታሎች ሁኔታው ከአቅማቸው በላይ በመሆኑ ጥቃቱ ወደተፈጸመባት ዶሪ ከተማ ትናንት የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረሱን አስታውቋል።

ከከተማዋ ባለሥልጣናት በቀረበ ጥያቄ መሰረት ወደአምስት መቶ ኪሎ ግራም ገደማ የሚመዝን የህክምና አቅርቦት በአስቸኳይ አድርሰናል ብሏል።

ባለፈው አርብ ሌሊቱ ላይ ጥቃቱ የተፈጸመው በቦርኪና ፋሶ የሳህል አካባቢ ከኒጀር ጋር በሚያዋስናት ድንበር አቅራቢያ ባለች መንደር መሆኑ ነው የተገለጸው። በጥቃቱ የተገደሉት እና የቆሰሉት ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው። ለጥቃቱ ኃላፊ ነኝ ያለ ወገን ባይኖርም ተንታኞች ግን የታላቁ ሰሃራ እስላማዊ መንግሥት (ኢዝላሚክ ስቴት ኢን ግሬተር ሳሃራ) የሚባለው ቡድን ሳይሆን አይቀርም ብለው ጠርጥረዋል።

እአአ በ 2015 በቦርኪና ፋሶ እና ከአልቃይዳ እና ከእስላማዊ መንግሥት ቡድኖች ጋር ቁርኝት ባላቸው ታጣቂ ቡድኖች መካከል ግጭት ከተጀመረ ወዲህ የአርብ ዕለቱ በተገደለው ሰው ብዛት ከፍተኛው መሆኑ ተገልጿል።

እአአ ከመጋቢት 2020 እስከ አለፈው ሚያዝያ ወር በነበረው የአንድ ዓመት ጊዜ ቦርኪና ፋሶ ውስጥ የደርሱት ግጭቶች በእጅጉ ቀንሰው የነበረ ሲሆን ከሚያዝያ ወር ወዲህ ሰባት ተከታታይ ጥቃቶች መድረሳቸው ታውቋል።

የቦርኪና ፋሶ የጸጥታ ተንታኝ ማሃማዱ ሳዋዶጎ ለቪኦኤ በሰጡት ቃል የታጠቁ ሽብርተኛ ቡድኖች ጉልበታቸውን እያፈረጠሙ መሆኑን የሚያመለክት እንደሆነ ገልጸዋል።

ቡድኑ ዮጋን ክፍለ ግዛትን ለረጅም ጊዜ ተዋግቶ የተቆጣጠራት ሲሆን ሽብርተኛ ቡድኖች ለእንቅስቃሴያቸው ገንዘብ ለማግኘት የሚያዘወትሩት የወርቅ ማዕድን የሚገኝበት አካባቢ ያለው በዚያ ክፍለ ሀገር መሆኑን ዜናው ጨምሮ አውስቷል።

XS
SM
MD
LG