በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የአፍሪካ ኅብረት የምርጫ ታዛቢዎች አዲስ አበባ ገቡ


የአፍሪካ ኅብረት ከኢትዮጵያ መንግሥት በደረሰው ጥያቄ መሠረት የአጭርና የረዥም ጊዜ የምርጫ ታዛቢዎች ቡድኖችን መላኩን የኅብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማህማት አስታወቁ።

የፊታችን ሰኔ 14 የሚካሄደውን አጠቃላይ ብሄራዊ ምርጫ የሚታዘቡት ከተለያዩ የኅብረቱ አባል ሃገሮች የተውጣጡ ስምንት አባላት የሚገኙበት የረዥም ጊዜ ክትትል ቡድን ትናንት ሐሙስ እና ከትናንት በስተያ አዲስ አበባ መግባቱን የአፍሪካ ኅብረት ዛሬ ባወጣው የፕሬስ መግለጫ አመልክቷል።

ቡድኑ በኢትዮጵያ ቆይታው ቁልፍ የሚባሉ የምርጫ ሂደቱ ክፍሎች ላይ ቅኝት እንደሚያደርግና ትንተናም እንደሚሰጥ መግለጫው ጠቁሞ ይህም በተለይ የፖለቲካውን አየር፣ የምርጫውን የህግ ማዕቀፍ፣ የምርጫ ዝግጅቱን ውጤታማነትና ግልፅነት እንዲሁም የአስተዳደርና የመገናኛ ብዙኃን ነፃነትንና በመላ ሂደቱ ውስጥም ለተሣትፎ መብቶች መከበር የሚሰጠውን ትኩረት ጨምሮ የዘመቻውን አካሄድ ሁኔታ እንደሚያካትት አስታውቋል።

የረዥም ጊዜ ታዛቢ ቡድኖች በሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች እንደሚሰማሩ የአፍሪካ ኅብረት ጠቁሞ ምርጫው ሊካሄድ ወደ አንድ ሳምንት ሲቀር ብርካታ የአጭር ጊዜ ታዛቢ ቡድኖች አዲስ አበባ እንደሚገቡ ገልጿል።

ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሠማራው የአፍሪካ ኅብረት ታዛቢ ተልዕኮ በኅብረቱ ድንጋጌዎች መሠረት በምርጫው ሂደት ላይ መረጃ የመሰብሰብና የመተንተን መብትና ችሎታ እንዳለው የፕሬስ መግለጫ በተለያዩ ጊዜዎች የወጡና የተፈረሙ ውሎችና መግለጫዎችን አጣቅሶ አስታውቋል።

XS
SM
MD
LG