በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ተማሪዎች በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ፈጣሪ መሆን ይችላሉ


ስቴም ሲነርጂ ባሰለጠናቸው ተማሪዎች የተሰራው በፀሀይ ብርሃን የሚሰራ የዳቦ መጋገሪያ
ስቴም ሲነርጂ ባሰለጠናቸው ተማሪዎች የተሰራው በፀሀይ ብርሃን የሚሰራ የዳቦ መጋገሪያ

ላለፉት አምስት አመታት በኢትዮጵያ የሚማሩ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች የሳይንስና ቴክኖሎጂ ትምህርት ላይ እንዲበረቱና የስራ ፈጠራ ክህሎታቸውን እንዲያዳብሩ ሲሰራ የቆየው ስቴም ሲነርጂ የተሰኘ ተቋም አሁን ደግሞ ተማሪዎች ሀገር ውስጥ የሚገኝ ጥሬ እቃ ተጠቅመው በፀሀይ ሀይል የሚሰራ የዳቦ መጋገሪያ እንዲያመርቱ አድርጓል።

ተማሪዎች በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ፈጣሪ መሆን ይችላሉ
please wait

No media source currently available

0:00 0:07:39 0:00


(ዝርዝሩን ከላይ ከተያያዘው ፋይል ያዳምጡ)

ከጀርመን ሀገር የተወሰደውና ባለፈው ሳምንት ለሙከራ እይታ የበቃው አዲሱ ቴክኖሎጂ፣ የፀሀይ ብርሀንን በ 5 ስኩዌር ሜትር ላይ ሰብስቦ በማሳረፍና ነፀብራቁ ወደ አንድ ቦታ እንዲያተኩር በማድረግ ሙቀት መፍጠር እንዲችል የሚያደርግ ነው - ሙቀቱ ደግሞ ወደ ዳቦ መጋገሪያውን በማጋል በቀላሉ ዳቦ መጋገር ያስችላል።

ይህን በሀገር ውስጥ የሚገኝ ጥሬ እቃን ብቻ በመጠቀም የተሰራ ቴክኖሎጂ የሰሩት ስቴም ሲነርጂ በተሰኘ ተቋም የሰለጠኑ የምህንድስና፣ የብየዳና መገጣጠም ሙያ ያላቸው ተማሪዎች ናቸው።

መቀመጫውን በአሜሪካን ሀገር አድርጎ የዛሬ ስድስት አመት የተመሰረተው ድርጅት ኢትዮጵያ ውስጥ የሚማሩ ተማሪዎች ከልጅነታቸው ጀምሮ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፍቅር እንዲኖራቸውና ተግባራዊ ልምምድ በማድረግ የፈጠራ ክህሎታቸውን እንዲያካብቱ የሚያደርግ ተቋም መሆኑን የድርጅቱ ዋና ስራ አስኪያጅና ፕሬዝዳንት የሆኑት አቶ ፀጋዬ ለገሰ ይገልፃሉ።

የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ሀይል እና ሂሳብ ትምህርቶች ላይ አተኩሮ የሚሰራው ተቋም በኢትዮጵያ የተለያዩ ክልሎች ውስጥ ከሚገኙ ዩንቨርስቲዎች ጋር በመተባበር ለአንደኛ እና ለሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች የሚያገለግሉ ስምንት ቤተ ሙከራዎችን ከፍቷል። አቶ ፀጋዬ እንደሚሉትም፣ ድርጅቱ በየአመቱ የሚያዘጋጀው የሳይንስ ውድድር ህፃናት የፈጠራ ችሎታቸውን እንዲያዳብሩ ያግዛል።

ስቴም ሲነርጂ በሳይንስ ትምህርት የሚያደርገው ጥረት አድጎ የዛሬ ሳምንት ድርጅቱ ባሰለጠናቸው ተማሪዎች የተሰራው በፀሀይ ብርሃን የሚሰራ የዳቦ መጋገሪያ ለዕይታ አቅርቧል። አቶ ይስሃቅ ኡኩሞ ሽታ በሙያቸው መሀንዲስ ሲሆኑ በአሜሪካን ሀገር የሚገኝ የኮንስትራክሽን ድርጅት የፕሮጀክት ማናጀር ሆነው ይሰራሉ። በስቴም ውስጥ ደግሞ በበጎ ፈቃደኝነት የቦርድ ሊቀመንበር ሆነው ያገለግላሉ፣ የቴክኖሎጂ ስራውንም በሀላፊነት ይመራሉ።

ይህ የዳቦ መጋገሪያ የመጀመሪያው የፈጠራ ውጤት ይሁን እንጂ አቶ ይስሃቅ ስቴም በቀጣይ የሚሰራቸው የፀሃይ ብርሃንን የሚጠቀሙ ቴክኖሎጂዎች እንዳሉ ያብራራሉ።

የስቴም ሲነርጂ ተቋም ዋና አላማ ተማሪዎች ስራ ፈጣሪ እንዲሆኑና በአካባቢያቸው የሚገኙ ቁሳቁሶችን ተጠቅመው የህብረተሰቡን ችግር መፍታት እንዲችሉ ማገዝ ነው። ድርጅቱ ባቋቋማቸው የቤተ ሙከራ ማዕከላት ተጠቃሚ በመሆናቸው የሳይንስ ችሎታቸውን ማዳበር የቻሉና ዛሬ ትልቅ ደረጃ መድረስ የቻሉ ተማሪዎችን ማፍራታቸውንም አቶ ይስሃቅ ይገልፃሉ።

አቶ ፀጋዬም ተማሪዎች የሳይንስና ቴክኖሎጂ ትምህርቶች ላይ ማተኮራቸው በዓለም ላይ ህይወትን እያቀለለ ያሉ ቴክኖሎጂዎችንና ለብዙ ችግሮች መፍትሄ ማምጣት የሚችሉ ፈጣሪዎች እንደሚያደርጋቸው ያሰምሩበታል።

ስቴም በአሁኑ ወቅት ችግር ፈቺ የሆኑ ፈጠራዎችን መስራት የሚያስችሉ የቴክኖሎጂ እና ምህንድስና ትምህርቶች ላይ ያተኩር እንጂ ሌሎች የሳይንስና የሂሳብ ትምህርቶች ላይም ድጋፍ ማድረጉን ይቀጥላል።

XS
SM
MD
LG