በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በትግራይ ክልል የልጆች መብቶች ጥሰት እየቀነሰ አይደለም- ዩኒሴፍ


በኢትዮጵያ የትግራይ ክልል ከሰባት ወራት በፊት የተቀሰቀሰውን ግጭት ተከትሎ በክልሉ ዙሪያ የሚደርሰው የልጆች መብቶች ጥሰት በስፋቱም ሆነ በከባድነቱ እየቀነሰ አይደለም ሲል ዩኒሴፍ ተናገረ።

የተመድ የህጻናት መርጃ ድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሄንሪየታ ፎር ባወጡት መግለጫ እስካሁን በክልሉ ጥበቃና እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ብቻቸውን ያሉ ወይም ከቤተሰብ የተነጠሉ 6000 ህጻናት ተመዝግበዋል ብለዋል። አስከትለውም የዩኒሴፍዋ ዋና ዳይሬክተር በደኅንነት ችግር ወይም ደግሞ የግጭቱ ተሳታፊ ወገኖች በጣሉዋቸው ገደቦች የተነሳ ልንደርስ ባልቻልንባቸው የክልሉ አካባቢዎች ሌሎችም እርዳታ የሚያስፈልጋቸው በርካታ ህጻናት ይኖራሉ ብለን እንሰጋለን ብለዋል።

የህጻናቱን ቤተሰቦች ፈልጎ ለማገናኘት የሚደረገውን ጥረት ውሱን የሆነው የቴሌኮሙኒኪሽን አገልግሎት፣ የማኅበራዊ ኑሮ ባለሙያዎች እጥረት እና ያለው የተደራሽነት ችግር ጥረታችንን እያደናቀፈው ነው ሲሉም አክለዋል።

በመቀጠልም ሴቶች እና ልጃገረዶች አሁንም የሚዘገንን ወሲባዊ ጥቃት ይፈጸምባቸዋል ያሉት የዩኒሴፍዋ ዋና ዳይሬክተር ግጭቱ ከጀመረ ወዲህ 540 የጥቃቶቹ ሰለባዎች የዩኒሴፍ ድጋፍ ተጠቃሚ ብለው የሆነ ሆኖ ባጠቃላይ ባለው የጸጥታ ሁኔታ እና የበቀል ጥቃት ይደርስብናል በሚል ፍርሃት በአጣዳፊ የሚያስፈልጋቸውን እንክብካቤና ድጋፍ ከመጠየቅ የሚቆጠቡ ብዙዎች ይኖራሉ ብለዋል።

ልጆች፣ ወላጆች እና ሌሎችም ጠባቂዎቻቸው የበቀል ጥቃት ይደርስብናል የሚል ከባድ ጭንቀት ላይ እንዳሉ ይናገራሉ። ታዳጊ ወንዶች ልጆች በውጊያው በሚካፈሉት ወገኖች በተዋጊነት እንመለመላለን ብለው ይሰጋሉ ያሉት ሄሪየታ ፎር በዘፈቀደ የሚፈጸመው እስርም መቀጠሉን አጋሮቻችን አሳውቀውናል ብለዋል።

በዚህ ግጭት እጅግ የከበደውን ዋጋ የሚከፍሉት ህጻናቱ ናቸው ያለው ዩኒሴፍ ሁሉም ወገኖች ችግር ላይ ላሉት ሲቪሎች ሁሉ በተለይም ለህጻናቱ የሚያስፈልጋቸው እርዳታ ሳይገደብ እና ሳይቋረጥ እንዲደርስ የመፍቀድ መሰረታዊ ግዴታቸውን እንዲያከብሩ እንጠይቃለን፥ ህጻናትን ከጥቃት ከብዝበዛ እና ከእንግልት ለመጠበቅ ከወላጆቻቸው ወይም ከጠባቂዎቻቸው እንዳይነጠሉ ለመጠበቅ የተቻላቸውን ሁሉ እንዲያደርጉ እንማጸናል ሲል ዩኒሴፍ ተማጽኖ አቅርቧል።

XS
SM
MD
LG