በትግራይ ክልል ባለፈው ሰኞ ማታ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች መጠለያዎችን የወረሩ ወታደሮች ከሁለት መቶ የሚበልጡ ሰዎችን በዘፈቀደ አፍሰዋል፣ ደብደባና ሌላም ያልተገባ የማንገላታት ተግባር አድርሰዋል ሲሉ በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ረድዔት አስተባባሪ ካትሪን ሶዚ ማውገዛቸውን የድርጅቱ ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱጃሪች ተናገሩ።
ቃል አቀባዩ በትናንት ዕለታዊ ገለጻቸው ሽሬ ከተማ በሚገኙት በአጠቃላይ ወደ 12000 የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች በተጠለሉባቸው “ጸሃዬ” እና “ወንፊቶ” ከተባሉ ካምፖች ታፍሰው የተወሰዱ ተፈናቃዮች ባስቸኳይ እንዲለቀቁ የተመድዋ የሰብዓዊ ጉዳዮች አስተባባሪ መጠየቃቸውን ቃል አቀባዩ አክለዋል።
በተፈጸሙት ከባድ የዓለም አቀፍ ሰብዓዊ ሁኔታ እና ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ ባፋጣኝ ምርመራ እንዲከፈት ፈጻሚውቹም ህግ ፊት እንዲቀርቡ ካትሪን ሶዚ ማሳሰባቸውን ስቴፋን ዱጃሪች አስታውቀው ድርጅታችን እና አጋሮቹ የሲቪሎች ደኅንነት መረጋገጥ በተመለከተ ከወታደራዊ አዛዦች ጋር በትብብር ለመስራት ዝግጁ ነን ብለዋል።
የተቀረውም የትግራይ ክልል ሰብዓዊ ሁኔታ አሁንም የእርዳታ ተደራሽነቱ እንደቀጠለ ነው፤ አብዛኛው ህዝብ በሚኖርበት በክልሉ ማዕከላዊ ዞን አሁንም አንድ ነጥብ ሚሊዮን ሰዎች በአመዛኙ ከእርዳታ ተደራሽነት ውጭ ናቸው ብለዋል።
የሰብዓዊ ረድዔት ሰራተኞች ሊደርሱ በቻሉባቸው አካባቢዎች ሁኔታው አስከፊ ነው የምግብ፣ የውሃ አቅርቦት የኤሌክትሪክ እና የጤና አገልግሎትን ጨመሮ ችግሩ አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንዳለ ነው የገለጹት። የምግብ እጠረቱም አሳሳቢ መሆኑን ገልጸው በቀጣዮቹ ጥቂት ወራት ውስጥ በአስቸኳይ ለችግሩ መፍትሄ ካልተሰጠ ብዛት ያለው ህዝብ ለአጣዳፊ የተመጣጠነ ምግብ ዕጦት እንደሚጋለጥ ተናግረዋል። የሰብዓዊ ረድዔት ተደራሽነት ደኅንነቱ በተጠበቀ፣ ባልተገደበ እና ቀጣይነት ባለው መንገድ እንዲጠናከር እና ለዚሁ ሥራ እስፈላጊ የሆነው የገንዘብ ድጋፍ እንዲሰጠን መጠየቃችንን እንቀጥላለን ሲሉ የተመድ ቃል አቀባይ አስታውቀዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከመጠለያ ካምፖቹ በመቶዎች የተቆጠሩ ሰዎች በወታደሮች ታፍሰው መወሰዳቸውን ከገለጹት ሪፖርቶች ተከትሎ የመንግሥታቱ ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ቃል አቀባይ ባባር ባሎች ዛሬ ዓርብ በጄኔቫ የኮሚሽኑ ጽሀፈት ቤት ባደረጉት ጋዜጣዊ ጉባዔ በግጭት ላይ በሚገኘው በትግራይ ክልል ለሲቪሎች ደኅንነት ጥበቃ እንዲደረግ ተማጽኖ አቅርበዋል።
ሁሉም ወገኖች የሲቪሎችን በግዴታ ከቀያቸው የተፈናቀሉትንም ጭምር ደኅንነት እንዲጠብቁ ደግመን ጥሪ እናቀርባለን፥ በግጩቱ የሚሳተፉት ወገኖች በሙሉ የተፈናቃዮች መጠለያዎችን ሲቪላዊ እና ሰብዓዊ ይዘት መገንዘብ ይገባቸዋል ብለዋል።
በዘገባዎች መሰረት ሰኞ ማታ የኤርትራ እና የኢትዮጵያ ወታደሮች ሽሬ ከተማ የሚገኙትን መጠለያ ካምፖች ወርረው በመቶዎች የተቆጠሩ ወጣት ወንዶች እና ሴቶች አፍሰው ወስደዋል፤ ባባር ባሎች ሲናገሩ ከተወሰዱት ውስጥ አንዳንዶቹ ጉዳዩን ለኢትዮጵያ መንግሥት ካሳሰበ በኋላ ተለቀዋል ብለዋል። የዩኤንኤችሲአሩ ቃል አቀባይ የታሰሩት ተፈናቃዮች ምን ያህል እንደነበሩ እና ያልተለቀቁት የት እንዳሉ በዝርዝር አልገለጹም።