የግብፅ ፕሬዚዳንት አብደል ፋታህ አል ሲሲ በጂቡቲ ጉብኝት እያደረጉ ናቸው። አሶሼየትድ ፕሬስ እንደዘገበው የፕሬዚዳንት ሲሲ ጉብኝት ዓላማ፣ ሃገራቸው ከኅዳሴ ግድብ በተያያዘ ከኢትዮጵያ ጋር ባላት ጭቅጭቅ፣ ከአፍሪካ ሃገሮች የበለጠ ትብብር ለማሰባሰብ በያዘችው ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ከጅቡቲ አቻቸው ጋር ተወያይተዋል።
ጅቡቲ እአአ በ1977 ነጻነቷን ካወጀች ወዲህ በግብፅ ርዕሰ ብሄር ስትጎበኝ ፕሬዚዳንት አል ሲሲ የመጀመሪያ ናቸው።
የግብፅ ፕሬዚዳንት ጽ/ቤት ባወጣው መግለጫ ፕሬዚዳንት ኤል ሲሲ እና የጅቡቲው ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦማር ጌሌ የኅዳሴ ግድብ አሞላል እና ኦፐሬሽን፣ የቀጣናው መረጋጋት በሚያስቀጥል፤ የሁሉንም ወገኖች ጥቅም በሚያስጠብቅ መንገድ ፍትሃዊና አሳሪ በሆነ ህጋዊ ሥምምነት መሰረት መከናወን ያለበት መሆኑን ተስማምተዋል ማለቱን ዘገባው ጨምሮ አትቷል።
የግብፅ ፕሬዚዳንት ከጅቡቲ አቻቸው ጋር ባደረጉት ጋዜጣዊ ጉባኤ
"የሁለቱን የዓባይ የታችኛው ተፋሰስ ሃገሮች ጥቅም እና መብት ባላከተተ መንገድ በቦታው ለብቻ በሚደረግ ውሳኔ የሚካሄደውን ሁኔታ እንዲቀበሉ የሚደረግ አንዳችም ሙከራ ተቀባይነት እንደማይኖረው አጥብቄ አስገንዝቤአለሁ ብለዋል።
ኤል ሲሲ ከጅቡቲ ፕሬዚዳንት ጋር ያደረጉት ውይይት ፍሬያማ እንደነበር ገልጸው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያው እና ወታደራዊ ትብብር ስለሚያደርጉበት መንገድ መወያየታቸውንም ጨምረው ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ሁለተኛውን ዙር የግድቡን ሙሌት በተያዘለት ዕቅድ መሰረት የማከናወን አቋሟን እና በሦስቱ ሃገሮች መካከል ያለው ልዩነትም መፍትሄ ማግኘት ያለበት በአፍሪካ ኅብረት ማቀፍ ሥር ብቻ መሆኑን በተደጋጋሚ አስታውቃለች።
ባለፈው ወር በሦስቱ ሃገሮች መካከል ኪንሻሳ ውስጥ በወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር አደራዳሬነት የተደረገው ድርድር ካለውጤት መጠናቀቁ ይታወሳል።