ዩናይትድ ስቴትስ ለትግራይ ክልል የጤና ቢሮ ከሠላሳ ሦስት በላይ ተሽከርካሪዎችና ከሦስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚገመት የህክምና መሳሪያዎች እና ቁሳቁስ እርዳታ መስጠቷ ተገለጸ።
ተሽከርካሪዎቹ በትግራይ ዙሪያ የተዘረፉ እና የወደሙ ህይወት አድን የጤና አገልግሎቶችን ለመስጠት አስፈላጊ መኪናዎችን ለመተካት የሚውሉ መሆናቸውን በኢትዮጵያ የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ባለፈው ሳምንት ሃሙስ የተሰጡት እርዳታዎች ዩናይትድ ስቴትስ በክልሉ በቀጠለው ግጭት ምክንያት ለተጎዱ ነዋሪዎች ወሳኝ የጤና እንክብካቤ በመስጠት ላይ ላሉት የክልሉ የጤና ሰራተኞች በዓለም አቀፍ ልማት ተራድዖ ድርጅቷ በኩል የቀጠለችው ድጋፍ አካል መሆኑን ኤምባሲው አመልክቷል።
ዩናይትድ ስቴትስ የለገሰቻቸው መኪናዎች የጤና ሰራተኞችን የጤና አገልግሎት ተደራሽነት ወደሌላቸው ማኅበረሰቦች ለማጓጓዝ፥ የህክምና ቁሳቁስ ለማድረስ እና የወሊድ አገልግሎት የሚያስፈልጋቸውን እናቶች ጨምሮ ልዩ ህክምና የሚያስፈልጋቸውን ታካሚዎች ለማጓጓዝ እንደሚውል ኤምባሲው አስረድቷል። በተለይ ከመኖሪያቸው ለተፈናቀሉ ማኅበረሰቦች ተንቀሳቃሽ የህክምና አገልግሎት ማድረስ ወሳኝ መሆኑን አያይዞ ጠቅሷል።
የዩኤስኤይድ የኢትዮጵያ ሚሽን ዳይሬክተር ሻን ጆንስ
"ዩናይትድ ስቴትስ እና አጋሮችዋ በትግራይ ክልል በተራዘመው ግጭት ምክንያት የተጎዱ ዜጎችን መርዳታቸውን በጽናት ይቀጥላሉ፥ አሁንም የተሰጡት ተሽከርካሪዎች እና የህክምና አቅርቦቶች በግጭቱ ምክንያት ከጤና አገልግሎት ተደራሽነት ውጭ ለሆኑት ህጻናት ሴቶች እና ቤተሰቦች ህይወት አድን አገልግሎት ያቀርባሉ" ብለዋል።