በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የብሊንከን የመካከለኛው ምሥራቅ ጉብኝት


የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን
የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን

እስራኤል እና ሃማስ ባለፈው ሳምንት ያደረጉትን የተኩስ አቁም ሥምምነት ለማጎልበት ወደመካከለኛው ምስራቅ የተጓዙት የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን በዛሬ ማክሰኞ የእየሩሳሌም ጉብኝታቸው፣ እስራኤል ራሷን ከጥቃት መከላከል መብቷ መሆኑን አጥብቀው አስገንዝበዋል።

ብሊንከን ከእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቢኒያሚን ኔታንያሁ ጋር ሆነው በሰጡት ቃል በውጊያው እስራኤልም ፍልስጥኤማውያንም ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል ካሉ በኋላ ለመጻኢው ጊዜ ተስፋ፣ መከባበር እና መተማመንን ለማስፈን ብዙ ሥራ መሰራት ይኖርበታል ሲሉ አሳስበዋል።

በሰው ላይ የሚደርሱ ጉዳቶች ብዙውን ጊዜ በቁጥር ደረጃ ዝቅ ተደርገው የሚገለጹ ቢሆንም በእያንዳንዷ ቁጥር የሚገለጸው አባት፣ እናት፣ ልጅ፣ አያት፣ ጓደኛ ሰብዓዊ ፍጡር ነው። ጥንታዊው የአይሁድ ሃይማኖታዊ ህግ እንደሚያስተምረውም፣ ህይወት ሲጠፋ የእስራኤላዊም ይሁን የፍልሥዔማዊ ህይወት መጥፋት ከመላው ዓለም መጥፋት የሚቆጠር ነው ብለዋል።

ዩናይትድ ስቴትስ ሃማስ በማይጠቀምበት መንገድ ጋዛን መልሶ ለመገንባት ዓለም አቀፍ ድጋፍ ለማሰባሰብ ትሰራለች ሲሉም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አክለው ገልጸዋል። አስከትለውም ጋዛ እና ዌስት ባንክ ለሚኖሩ ፍልስጤማውያን የኢኮኖሚ ዕድሎችን ለማጎልበት እንሰራለን ሲሉ ቃል የገቡት የዩናይትድ ስቴትሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ይህ ሲሆን እስራኤልንም ፍልስጥኤሞችንም የሚጠቅም የተረጋጋ ድባብ ሊያመጣ ይችላል ብለዋል።

ብሊንከን ዛሬ ከፍልስጤም ፕሬዚደንት ማህሙድ አባስ እና ከጠቅላይ ሚኒስትር ማሃማድ ሲታዬህ ጋር ራማላህ ውስጥ ሲገናኙ ዩናይትድ ስቴትስ የምታሰጠውን እርዳታ ይፋ ሊያደርጉ አቅደዋል።

ኔታንያሁ በበኩላቸው ዩናይትድ ስቴትስን ስለድጋፉዋ አመስግነው፣ ሃማስን ተኩስ አቁሙን እንዲያከብር አስጠንቅቀዋል። ሃማስ ተኩስ አቁሙን አፍርሶ እስራኤል ላይ ጥቃት የሰነዘረ እንደሆን እጅግ ከባድ አጸፋ ይከተለዋል ብለዋል ኔታንያሁ።

ኔታንያሁ በተጨማሪም የዩናይትድ ስቴትስን የኤራንን የኒውክሊየር መርሃ ግብር የሚመለከተው ዓለም አቀፍ ሥምምነትን ተመልሳ የመቀላቀል አካሄድ እንደሚቃወሙ አስረድተዋል።

አንተኒ ብሊንከን በዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚንስትርነት የመጀመሪያቸው በሆነው የመካከለኛው ምስራቅ ጉዟቸው ወደግብጽ በመጓዝ እስራኤል እና ሃማስ ተኩስ አቁም ስምምነት እንዲያደርጉ ከሸመገሉት ከፕሬዚደንት አብደልፋታህ አል ሲሲ እና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሳሜህ ሹክሪ ጋር ይነጋገራሉ።

XS
SM
MD
LG