በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሴኔት ሪዞልሽን 97 እና ኢትዮጵያ


.
.

የዩናይትድ ስቴትስ የህግ መወሰኛ ምክር ቤት፣ ሴኔት ሪዞልሽን 97 በተሰኘው የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ ለማሻሻል መወሰድ የሚገባቸውን ርምጃዎች በዘረዘረው ረቂቅ ውሳኔ ላይ በሙሉ ድምጽ መስማማቱ ታውቋል።

የውሳኔው ሰነድ እንደ መንደርደሪያነት የኢትዮጵያን እና የዮናይትድ ስቴትስን አንድ ክፍለ ዘመን የተሻገረ ጠቃሚ ግንኙነት ዘክሯል። ከሰሃራ በታች ያለውን የአፍሪካ ቀጠና ደህንነት በማስጠበቅ እና በማረጋጋት ረገድ ያላትን ቁልፍ ሚና እና ተሳትፎም አንስቷል።

በትግራይ ክልል የተቀሰቀሰው ግጭት ፣አሁን ላይ በሚታየው ቀጠናዊ እና ዓለማቀፍ ውስብስብ ውጥረት ላይ የታከለ ተጨማሪ ፈታኝ መሆኑን ለማሳየት ፣ በኢትዮጵያ ፣ ሱዳን እና ግብጽ መካከል ያለውን የህዳሴ ግድብን የተመለከተ ድርድር፣ የአልሸባብ ቡድን ጥቃት ስጋት፣ሱዳን እና ኢትዮጵያ የገቡበትን የድንበር ይገባኛል ውዝግብ እንዲሁም ያልጠናውን የጎረቤት ሀገር ሱዳን የሽግግር እና የሰላም ሂደትን ጠቅሷል።

በሪፐብሊካኑ የአይዶዋ እንደራሴ ሴናተር ጄምስ ኢ ሪስክ አማካይነት ለህግ መወሰኛ ምክር ቤቱ መጋቢት ወር ላይ በቀረበው ረቂቅ ውሳኔ መሰረት በኢትዮጵያ መንግስት እና በትግራይ ህዝቦች ነጻነት ግንባር መካከል ያለው ፖለቲካዊ ውጥረት ተቀባይነት የለውም። በሰላማዊ ሰዎች ላይ የደረሱ ማናቸውም የኃይል እርምጃዎችን ያወግዛል።ኤርትራ ጦሯን ከኢትዮጵያ እንድታስወጣ ጥሪ ከማቅረብ በተጨማሪ በኤርትራም ጦርም ሆነ በሌላ በክልሉ ውስጥ ባለ ማንኛውም ኃይል የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን፣ ግድያ፣ ዝርፊያ ፣ አስገድዶ መድፈር እና ሌሎችንም ወንጀሎችን ያወግዛል።

በትግራይ ክልል በጠላትነት መፈላለግ በአስቸኳይ ቆሞ ሁሉም ወገኖች የሰብዓዊ መብቶች ለመጠበቅ እንዲሰሩም ጥሪ አቅርቧል። ከዚህ በተጨማሪ የሚመለከታቸው የዮናይትድ ስቴትስ ተቋማት በትግራይ ክልል ያለው ግጭት ይቆም ዘንድ የሚያበረታቱ እንዲሁም ሰብዓዊ ድጋፎችን ለመስጠት የሚያግዙ እርምጃዎችን እንዲወስዱ ጥሪ አቅርቧል ።

ከመንግስት ውጪ የሆኑ ታጣቂ ቡድኖችን ጨምሮ ተጨማሪ ብሄር ተኮር ጥቃቶችን ለማስቆም እና ጤናማ ፉክክር ያለበት ብዘሐ- የፖለቲካ ፓርቲ ዲሞክራሲን ለማበረታታት ሁሉን ዐይነት ዲፕሎማሲያዊ፣ ልማታዊ እና ህጋዊ መሳሪያዎች ለጥቅም እንዲውሉም አሳስቧል።

10 አንቀጾች ያሉት የምክር ቤቱን አባላት ሙሉ ተቀባይነት ያገኘው ውሳኔ አክሎም ኢትዮጵያ በእስር ላይ ያሉ የተቃዋሚ ፓለቲካ አመራሮች፣ ደጋፊዎች እና ለውጥ አቀንቃኞች ፣ በስራቸው ምክንያት ለእስር የተዳረጉ ጋዜጠኞችን እንድትፈታ ጠይቋል።የኢትዮጵያዊያንን ራስን የመግለጽ መብት እና ፖለቲካዊ ተሳትፎ ካለ ብሄር ፣ አስተሳሰብ፣ እና ፖለቲካ አቋም አድሎ እንድታስከብርም ጠይቋል።

ከላይ ከተጠቀሱት ጉዳዮች በተጨማሪ ተያያዥ ጉዳዮች ውሳኔው አነሳስቷል። ከእነዚህ መካከል ሰብዓዊ ድጋፎች የሚሰራጩበትን ፣ የተቋረጡ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች ዳግም ስራ የሚጀምሩበትን፣ ሀገራዊ ንግግር እና መግባባትን የሚፈጥሩ መደላድሎችን ሁሉም ተፋላሚዎች ይገነቡ፣ይፈቅዱ ፣ ያረጋግጡ ዘንድ ጥሪ አድርጓል።

XS
SM
MD
LG