የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሁለተኛው ዙር የኅዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት የግብጽ ፍላጎት ላይ ተፅዕኖ እንደማያሳድር መግለጻቸው ጥሩ ጅማሮ እና የኢትዮጵያን አቋም የሚደግፍ ነው ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ተናገሩ፡፡
አምባሳደር ዲና ዛሬ በሰጡት መግለጫ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሳሚ ሹክሪ ገለፃ ግብጽ በኅዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት ዙሪያ ቀደም ሲል ታራምድ የነበረውን አቋም በመቀየር ኢትዮጵያ የምታራምደውን አቋም ወደሚደግፍ ሃሳብ መሸጋገሯን የሚያመላክት መሆኑን ጠቅሰዋል።
በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት እና የውስጥ ጉዳይ ላይ በተለያየ መልኩ ጣልቃ ገብነት እየተደረገ ነው ያሉት አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፣ ኢትዮጵያ የኅዳሴ ግድቡን የውሀ ሙሌት አታካሂድም በሚል የተለያዩ ጫናዎች ሲደረጉ መቆየታቸውንና አሁን ላይ ጫናዎቹ እየቀነሱ መጥቷል ብለዋል።
ሁለተኛው ዙር የኅዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት የግብጽ ፍላጎት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አንደማይኖረው እንተማመናለን ያሉት የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሜህ ሹክሪ ግብፅ በአስዋን ግድብ ያላት የውሃ ክምችት መተማመን እንደፈጠራላት ተናግረዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት በአፍሪካ ህብረት ከሚመራው የሦስትዮሽ ውይይት እና ከአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ ከአንድ የቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ መሆኑን ግብጽ ኢንዲፔንዳንት ጋዜጣን የጠቀሰው የአገር ውስጥ የዜና ማሰራጫዎች ዘግቧል።
ግብጽ ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ዙር የውሃ ሙሌት ከማከናወኗ በፊት ጀምሮ ሙሌቱ የውሃ እጥረት እንዲከሰት ያደርጋል በሚል ሂደቱን ስትቃወም ቆይታለች። አሁንም ኢትዮጵያ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት ከማከናወኗ በፊት በተለያዩ መንገዶች እና ውይይቶች ተመሳሳይ ቅሬታ ስታቀርብ መቆየቷ የሚታወስ ነው።