በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የእስራኤል እና የሃማስ ታጣቂዎች ግጭት አስረኛ ቀን


በጋዛ ሰርጥ ውስጥ እስራኤል እና የሃማስ ታጣቂዎች ግጭት ዛሬም ለአስረኛ ቀን ቀጥሏል

በጋዛ ሰርጥ ውስጥ እስራኤል እና የሃማስ ታጣቂዎች ግጭት ዛሬም ለአስረኛ ቀን ቀጥሏል። ሁለቱ ወገኖች የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲያደርጉ ለመሸምገል የቀጣናው እና ዓለም አቀፍ ወገኖች በተደጋጋሚ ያደረጉት ጥረት አልተሳካም።

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ ለውጭ ሃገር ዲፕሎማቶች ባደረጉት ንግግር

“በአሁኑ ወቅት የያዝነው ጥቃትን በኃይል የመመከት እርምጃ ነው" በማለት ድጋፍ ጠይቀዋል።

ሀገራቸው ጋዝ ላይ እያካሄደች ባለው የአየር ጥቃት ላይ የሚሰነዘሩ ነቀፋዎችን ውድቅ ያደረጉት ኔታንያሁ ኃይሎቻችን በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ የተቻላቸውን ሁሉ ጥንቃቄ ያደርጋሉ ብለዋል።

“ኃይሎቻችን ለሚሰነዘሩት ጥቃቶች እጅግ ከፍተኛ በሆነ ጥንቃቄ አጸፋ ጥቃት ያደርሳሉ፤ ነገር ግን ከዒላማ ውጭ ምንም ዐይነት ጉዳት እንደማይደርስ እርግጠኛ መሆን አይቻልም” ብለዋል።

የፍልስጥዔም ፕሬዚደንት ማህሙድ አባስ በበኩላቸው በቴሌቭዢን ባደረጉት ንግግር

"እስራኤል ጋዛ ውስጥ የምትፈጽመው የተደራጀ መንግሥታዊ ሽብርተኝነት እና የጦር ወንጀል” ሲሉ የገለጹት ድርጊት በዓለም አቀፍ ህግ የሚያስቀጣት ነው ሲሉ አውግዘዋል።

ፍልስጥኤማውያን እንዲህ ያሉትን ወንጀሎች የሚፈጽሙት ዓለም አቀፍ ህግ ፊት ከማቅረብ ወደኋላ አይሉም ሲሉ ማህሙድ አባስ አክለዋል።

ማህሙድ አባስ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሚደገፈው የፍልስጥዔም አስተዳደር ፕሬዚደንት ሲሆኑ ሃማስ እአአ 2007 ጋዛን ሲቆጣጠር የእሳቸውን አስተዳደር ሃይሎች እንዳስወጣ ይታወሳል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ኤክስፐሮቶች ያሰባሰበ ቡድን እስራኤል ጋዛ ውስጥ ህዝብ በብዛት በሚኖርባቸው አካባቢዎች የምትፈጽመው የአየር ድብደባ ሲቪሎች እና በሲቫላዊ ንብረቶችን ሳይለይ የሚፈጸም ከመጠን ያለፈ ጥቃት ነው ብለውታል። የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዥ በበኩላቸው ጋዛ ውስጥ እጅግ የከበደ ሰብዓዊ ስቃይ፣ የመኖሪያ ቤቶች እና ወሳኝ የመሰረተ ልማት ተቋማት ውድመት እየደረሰ ነው ብለው፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በዚያ የመንግሥታቱ ድርጅት ለሚያካሂዳቸው ፕሮግራሞች የገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርግ ተማፅነዋል።

ፈረንሳይ ውጊያው እንዲቆም የሚጠይቅ ውሳኔ ከግብጽ እና ከዮርዳኖስ ጋር በመተባበር ለተባበሩት መንግሥታት የጸጥታ ምክር ቤት አቅርባለች።

XS
SM
MD
LG