በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የቶኪዮ ኦሊምፒክስ እንዲሰረዝ ተጠየቀ


ጃፓን ውስጥ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እያሻቀበ በመምጣቱ የቶኪዮ ኦሊምፒክ እንዲሰረዝ የሃገሪቱ የህክምና ባለሙያዎች ማህበር ጠየቀ።

አምና በዓለም አቀፍ ኮቪድ-19 ምክንያት ዘግይቶ የተዘጋጀው ውድድር ሊከፈት ሦስት ወር ያህል ነው የቀረው። የቫይረሱ ሥርጭት እየበረታ በመምጣቱ አንድ ትልቅ የጃፓን የህክምና ባለሙያዎች ማኅበር ውድድሩ እንዲሰረዝ ጠይቋል።

ማኅበሩ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዮሺሂዴ ሱጋ ትናንት ሰኞ በላከው ግልጽ ደብዳቤ የቶኪዮ ሆስፒታሎች ከዓቅማቸው በላይ እየሆነባቸው ነው ሲል አስጠንቅቋል

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ውድድሩን ማካሄድ አስቸጋሪ እንደሚሆን እና መሰረዝ እንዳለበት ዓለም አቀፉን የኦሊምፒክ ኮሚቴ እንዲያሳምኑ ስድስት ሽህ ዶክተሮች እና ሆስፒታሎች ያሉት ማኅበር ጠይቋል።

በሀገሪቱ የቫይረሱ ስርጭት በመባባሱ ዋና ከተማዋ ቶኪዮ እና ሌሎችም ክፍለ ሃገሮች ውስጥ አስቸኳይ ጊዜ ታውጇል።

ይህንኑ ተከትሎም ህዝቡ ውድድሩ በጠቅላላው መሰረዝ አለበት የሚል ጥያቄ እያነሳ ነው

በኮቪድ-19 ምክንያት የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በአምስት ነጥብ አንድ ከመቶ መቀነሱ ተዘግቧል።

በሌላም በኩል በፋይዘር እና በሞደርና ኩባኒያዎች የተሰሩት ክትባቶች መጀመሪያ ላይ ህንድ ውስጥ በተከሰቱት በሁለቱ የኮሮናቫይረስ ዝርያዎች ላይ በከፍተኛ ደረጃ የሚሰሩ መሆናቸውን የዩናይትድ ስቴትስ ሳይንቲስቶች ተናገሩ።

የፋይዘሩ ክትባት መጀመሪያ ላይ መቀመጥ አለበት በተባለው ከፍተኛ ቅዝቃዜ መጠን ከፍ በሚል ሁኔታ ረዘም ላለ ጊዜ መቀመጥ የሚችል መሆኑን የአውሮፓ ህብረት የመድሃኒት ተቆጣጣሪ ድርጅት አስታወቀ። ያልተከፈቱ ክትባቶች ከዜሮ በታች በሰባ ወይም ሰማኒያ ዲግሪ ሴልሲየስ በሆነ ከፍተኛ ቅዝቃዜ ሳይሆን ከሁለት እስከ ስምንት ዲግሪ በሆነ የሙቀት መጠን ከአምስት እስከ ሰላሳ ቀን መቀመጥ እንደሚችል አስታውቋል። ይህ መታወቁ የክትባት ማዳረሱ ደረጃ ዝግ ባለባቸው የህብረቱ አባል ሃገሮች ክትባቱን ፈጥኖ ለማቅረብ እንደሚያግዝ ተጠቁሟል።

በዓለም ዙሪያ የኮሮናቫይረስ ተጋላጮች ቁጥር ከ163 ነጥብ 6ሚሊዮን ማለፉን የጃንስ ሆፕኪንስ የመረጃ ማዕከል አሃዝ ያሳያል። ለህልፈት የተዳረጉት ሰዎች ቁጥር ደግሞ ከሦስት ነጥብ ሶስት ሚሊዮን አልፏል። በሁለቱም ከፍተኛውን ቁጥር እንደያዘች ባለችው በዩናይትድ ስቴትስ የቫይረሱ የተረጋገጠው የተጠቂዎች ቁጥር ከሰላሳ ሁለት ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን የሞቱት ሰዎች ደግሞ ከአምስት መቶ ሰማኒያ ስድስት ሽህ ሶስት መቶ ሃምሳ ማለፉን መረጃው አስታውቋል።

XS
SM
MD
LG