በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ሰብዓዊ ርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ተረጂዎች የእርዳታ ድርጅቶችን ተደራሽነት ወታደራዊ ኃይሎች የሚፈጽሙት የተረጋገጠ የማስተጓጎል አድራጎት እየጨመረ መምጣቱ ዩናይትድ ስቴትስን በእጅጉ አሳስቧታል ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን አስታወቁ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብሊንከን ቅዳሜ ባወጡት መግለጫ ይህ ተቀባይነት የሌለው ባህሪ በክልሉ አጣዳፊ እርዳታ የሚስፈልጋቸውን አምስት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ዜጎች ይብሱን የከፋ አደጋ ላይ የሚጥል ነው ብለዋል።
የኤርትራ እና የኢትዮጵያ መንግሥታት አስፈላጊውን እርምጃ በሙሉ በመውሰድ ኃይሎቻቸው ይህንን መወገዝ የሚገባው አድራጎት ማቆማቸውን እንዲያረጋግጡ ዩናይትድ ስቴትስ ጥሪዋን ታስተላልፋለች ብለዋል።
በተጨማሪም ሁሉም ወገኖች ሲቪሎችን ከጥቃት መጠበቅ፣ ግጭቶችን ማቆም እና እጅግ አጣዳፊ ችግር ላሉት ሰዎች እርዳታ እንዲደርስ መፍቀድን ጨምሮ በዓለም አቀፍ ሰብዓዊ ህግጋት ያሉባቸውን ግዴታዎች በሙሉ እንዲያከብሩ እናሳስባለን ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን የኢትዮጵያ መንግሥት የዚህ ጉዳይ አመራሩን በመውሰድ በክልሉ በጠቅላላ የሰብዓዊ ረድዔት ድርጅቶች በተሟላ እና ባልተደናቀፈ መንገድ መንቀሳቀስ የሚችሉበትን ሁኔታ በአስቸኳይ ማመቻቸት አለበት ብለዋል።
ትግራይ ውስጥ የታጠቁ ኃይሎች በሲቪሎች ላይ ጾታ ተኮር ጥቃቶችን እና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ጨምሮ የግፍ አድራጎቶች እንደሚፈጽሙ የተረጋገጡ ሪፖርቶች አሉ ያሉት ሚኒስትር ብሊንከን በተለይ በኤርትራ የመከላከያ ኃይሎች እና በአማራ ክልል ኃይሎች የሚፈጸሙት ከሁሉም አስከፊዎቹ ድርጊቶች ናቸው ሲሉ አክለዋል።
የኤርትራ ወታደሮች አሁንም ትግራይ ክልል ውስጥ መኖራቸው የኢትዮጵያን መረጋጋት እና ብሄራዊ አንድነቷን ይጎዳል ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን የኤርትራ መንግሥት ኃይሎቹን እንዲያስወጣ በድጋሚ እንጠይቃለን ብለዋል። አያይዘውም የኤርትራ እና የኢትዮጵያ መንግሥታት ወታደሮቹ እንደሚወጡ በተደጋጋሚ ቃል የገቡ ቢሆንም እስካሁን ያን ተፈጻሚ የሚያደርግ እንቅስቃሴ የለም ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥትም የአማራ ክልል ኃይሎችን ከትግራይ ክልል እንዲያስወጣ የምዕራባዊ ትግራይ አካባቢ በክልሉ የሽግግር አስተዳደር ቁጥጥር ስር መዋሉን እንዲያረጋግጥ እንጠይቃለን ያለው የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መግለጫው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና ፕሬዚደንት ኢሳያስ አፈወርቂ የግፍ አድራጎቶች የፈጸሙትን በሙሉ በተጠያቂነት መያዝ አለባቸው ብሏል።