በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የኮቪድ-19 ክትባት


የኮቪድ-19 ክትባት በፍትሃዊ መንገድ እንዲዳረስ የተዋቀረው ድርጅት ኮቫክስ በእጁ ያለው ክትባት እያለቀበት መሆኑ ተገልጿል።

የዚህ ችግር አመዛኙ ምክንያት የህንዱ ሴረም ኢንስቲቲዩት ለዓለም ሊያቀርብ ቃል ገብቶ የነበረውን ክትባት በሀገር ውስጥ ባለው የከበደ የክትባት ፍላጎት የተነሳ ለበርካታ ወራት ማቅረብ ሳይችል በመቅረቱ መሆኑ ተገልጿል።

ለኮቫክስ ክትባቶቹን እየገዛ የሚያከፋፍለው ዩኒሴፍ ሲሆን የዩኒሴፍ ዋና ድሬክተር ሄንሪየታ ፊዮር በሰጡት ቃል ሃገሮች ለኮቫክስ የገንዘብ ድጋፍ ሊሰጡ የገቡትን ቃል ተግባራዊ ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበው ያ ብቻ ሳይሆን ያላቸውን ትርፍ ክትባትም እንዲለግሱ ጥሪ አቅርበዋል።

አያያዘው የዩኒሴፍዋ ዋና ሥራ አስኪያጅ የቡድን ሰባት እና የአውሮፓ ህብረት አባል ሃገሮች በመጪዎቹ ሰኔ ሃምሌ እና ነሃሴ ወራት ከሚያጠራቅሙት የክትባት መጠን ለራሳቸው ህዝብ የሚያስፈልገውን አስቀምጠው ሃያ ከመቶውን ብቻ እንኳን ለሌሎች ሃገሮች ቢያካፍሉ በጠቅላላው 153 ሚሊዮን ክትባት ሊለግሱ እንደሚችሉ አሃዛዊ ግምገማዎች አሳይተዋል ብለዋል።

በሌላም በኩል ህንድ ዛሬ ሰኞ ማታ ምዕራባዊ የባህር ጠረፍ ግዛትዋ በባህር ማዕበል እንደሚመታ ተተንብይዋል። በዚህም የተነሳ በብዙ ሽዎች የተቆጠሩ ነዋሪዎች አካባቢውን ለቅቀው በሌላ ስፍራ መጠለያ ውስጥ እንዲገቡ ተደርጓል።

የአካባቢው የኮቪድ-19 ምርመራዎች እና የክትባት መርሃ ግብር የተቋረጠ ሲሆን ለሳምንታት በየቀኑ በመቶ ሽሆች የተቆጠሩ ሰዎች ለኮሮናቫይረስ እየተጋለጡ ባሉባት ሃገር ብዛት ያለው ሰው መጠለያ ውስጥ መቀመጡ የቫይረሱን መዛመት ያባብሰዋል የሚል ስጋት ፈጥሯል።

ይህ በእንዲህ እያለ እስራኤል ጋዛ ላይ የምታካሂደውን የአየር ጥቃት በመሸሽ ነዋሪዎች በየመጠለያው በተፋፈገ ሁኔታ መሸሸጋቸው የቫይረሱን ስርጭት እንደሚያባባሰው የረድዔት ድርጅቶች እያስጠነቀቁ ናቸው። በጥቃቶቹ ምክንያት የየኮሮናቫይረስ ምርመራ እና የክትባት መርሃ ግብሮች ተቋርጠዋል።

ዶክተር አንተኒ ፋውቺ
ዶክተር አንተኒ ፋውቺ

የዩናይትድ ስቴትስ ከፍተኛው የተላላፊ በሽታዎች አዋቂው ዶክተር አንተኒ ፋውቺ በሀገሪቱ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከነጮች ይበልጥ ነጭ ያልሆኑት ማኅበረሰቦች በከፋ ሁኔታ መመታታቸው፤ ሊካድ የማይችለውን የዘረኝነት ውጤት ገሃድ አውጥቶታል ሲሉ ተናገሩ ።

ዶ/ር ፋውቺ ትናንት ዕሁድ በአትላንታ ኤመሪ ዩኒቨርስቲ የተማሪዎች ምረቃ ሥነ ስርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር ጥቁሮች፣ ትውልደ ላቲን አሜሪካ እና ቀደምት አሜርካውያን ከነጮች ይበልጥ በስራቸው ላይ መገኘት ያለባቸው በሚባሉ የሥራ መስኮች የተሰማሩ በመሆናቸው ለቫይረሱ በይበልጥ የተጋለጡ መሆናቸውን አስረድተዋል። ከዚያም በተጨማሪ እነዚህ ማኅበረሰቦች በብዛት እንደስኳር በሽታ እና የደም ግፊት እንዲም ከልክ በላይ የሆነ የሰውነት ክብደት የመሳሰሉ ችግሮች የሚጠቁ በመሆናቸው በኮቪድ-19 ለከፋ ህመም ለመዳረግ የተጋለጡም ናቸው ብለዋል።

ተመራቂዎቹ ላለው የእኩልነት መዛባት መፍትሄ በመፈለግ እንዲሳተፉ ዶክተር ፋውቺ ጥሪ አቅርበውላቸዋል።

XS
SM
MD
LG