ምስራቃዊ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ዳርክሳይድ የሚባሉት የሩስያ የኮምፒዩተር ሰርሳሪዎች አደረሱት በተባለው ጥቃት ሳቢያ ለስድስት ቀናት ተሽመድምዶ የነበረውና ነዳጅ ቀጂዎችን አስግቶ የነበረው የነዳጅ መስመር ነዳጅ ማከፋፈል ጀምሯል።
ትናንት ፕሬዚደንት ጆ ባይደን መኪና አሽከርካሪዎችን
"ይሄ ጊዜያዊ ችግር ነው አትሸበሩ፣ በሚቀጥሉት ቀናትም ከሚያስፈልጋችሁ በላይ ነዳጅ አትቅዱ” ሲሉ ተማጽነዋል። ባለቢንዚን ማደያዎችንም አጋጣሚውን ተጠቅማችሁ ሸማቹ ላይ ዋጋ እንዳትጨምሩ በማለት አስጠንቅቀዋል።
ኮሎኒያል ፓይፕላይን የተባለው ኩባኒያ የነዳጅ መስመሩን ሥርዓት ለማስቀጠል መጠነ ሰፊ ሥራ ተሰርቷል። እስከ ዕኩለ ቀን ባለው ጊዜ ሁሉም የምናገለግላቸው ጣቢያዎች ነዳጅ ይቀርብላቸዋል ብሏል።
ይህ በዚህ እንዳለ በጃፓን ቶሺባ ኩባኒያ የአውሮፓ ቅርንጫፍ ላይ የተፈጸመውን ሳይበር ጥቃት ያደረሰው ዳርክሳይድ የተባለው ቡድን ነው ተብሎ መወንጀሉን የሀገሪቱን የዜና ማሰራጫ ኤንኤችኬን ጠቅሶ ሮይተር ዘግቧል።
ኮሎኒያል ፓይፕላይን ኩባኒያ ባለፈው ሳምን አርብ ለኮምፒዩተር ሰርሳሪዎቹ አምስት ሚሊዮን ዶላር ከፍሎ የነዳጅ መስመሩን ሥርዓት ያመሳቀለውን ጥቃት የሚቀለብስበትን መንገድ መቀበሉን ሆኖም ውጤታማ ሳይሆን መቅረቱን ብሉምበርግ ዘግቦ ነበር።
ኩባኒያው ለሰርሳሪዎቹ ገንዘብ መክፈሉን ወይም አለመክፈሉን በተመለከተ የተናገረው ነገር የለም። ፕሬዚዳንት ባይደንም ትናንት ተጠይቀው የምሰጠው አስተያየት የለኝም ብለዋል።