በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የእስራኤል የምድር ጦር የአየር ሃይሉ በጋዛ ሰርጥ እያካሄደ ያለውን ጥቃት መቀላቀሉ ተገለጸ


ከእስራኤል በሚያዋስነው የጋዛ ድንበር አካባቢ ግጭት አምስተኛ ቀኑ
ከእስራኤል በሚያዋስነው የጋዛ ድንበር አካባቢ ግጭት አምስተኛ ቀኑ

የእስራኤል የምድር ጦር ዛሬ ዓርብ ማለዳ የአየር ሃይሉ በጋዛ ሰርጥ እያካሄደ ያለውን ጥቃት መቀላቀሉን የሃገሪቱ የጦር ሃይል አስታወቀ።

ቀደም ብሎ የእስራኤል የመከላከያ ሃይል በትዊተር ባወጣው መግለጫ ወታደሮቹ ጋዛ ውስጥ ጥቃት እያካሄዱ ነው ካለ በኋላ ያን አስተካክሎ ወታደሮቻችን እስራኤል ውስጥ ሆነው ወደጋዛ መድፍ እየተኮሱ ናቸው ብሏል።

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ትናንት ሃሙስ ባወጡት መግለጫ ለሃማስ በሰጡት ጥብቅ ማስጠንቀቂያ ሃማስና ሌሎቹም አሸባሪ ድርጅቶች እጅግ ከባድ ዋጋ እንደምናስከፍላቸው ተናግሬያለሁ፣ አሁንም ይዘናል፣ ወደፊትም በብሩቱ ሃይል እንቀጥላለን ብለዋል።

ከእስራኤል በሚያዋስነው የጋዛ ድንበር አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች የእስራኤል ወታደሮችን በአካባቢው እንዳላዩ አረጋግጠዋል። ሆኖም ከባድ የመድፍ እና የእየር ድብድባ እየተካሄደ መሆኑ ገልጸዋል።

ዛሬ ግጭቱ አምስተኛ ቀኑን የያዘ ሲሆን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታ ምክር ቤት ተነገ ወዲያ ዕሁድ ስብሰባ አድርጎ ሊነጋገር ስምምነት ላይ መድረሱ ተገልጿል። ቀደም ሲል ስብስባውን ለማቀድ የተደረጉ ጥረቶች ዩናይትድ ስቴትስ ባሰማችው ስጋት ምክንያት ዘግይቶ እንደነበር ተመልክቷል።

በተመድ የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድ በትዊተር ባወጡት ቃል

"ዩናይትድ ስቴትስ ውጥረቶቹን ለማርገብ በከፍተኛው ደረጃ የተያዘ ንቁ የዲፕሎማሲ ጥረቶቿን ትቀጥላለች” ብለዋል።

በውጊያው ቢያንስ 27 ህጻናት እና 11 ሴቶችን ጨምሮ 103 ፍልስጤማውያን መገደላቸውን የጋዛ የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል። 530 ሌሎች ሰዎች መቁሰላቸውንም አክሎ አመልክቷል። ሰባት እስራኤላውያን አንድ የስድስት ዓመት ልጅ ጨምሮ በሮኬት ጥቃቶች መገደላቸውም ታውቋል።

XS
SM
MD
LG