በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በእስራኤል የፀጥታ ኃይሎች እና በሃማስ መካከል ውጊያው ተባባሷል


በእስራኤል የፀጥታ ኃይሎች እና በሃማስ መካከል የተፈጠረ ግጭት
በእስራኤል የፀጥታ ኃይሎች እና በሃማስ መካከል የተፈጠረ ግጭት

ዛሬ እየሩሳሌም እና ጋዛ ሰርጥ ውስጥ ቢያንስ አርባ ሰዎች መገደላቸው ተዘግቧል። ዛሬ ማለዳ እስራኤል የፖሊስ እና የጸጥታ ተቋማትን ዒላማ ያደረገ የአየር ድብደባ ያካሄደች ሲሆን መኖሪያዎችና ቢሮዎች ያሉበት አንድ ህንፃ በአየር ድብድባው ከባድ ጉዳት ደርሶበታል። በወቅቱ ህንጻው ውስጥ ሰው እንዳልነበር ተዘግቧል።

ትናንት ማክሰኞ እስራኤል ባደረሰችው የአየር ድብደባ መኖሪያዎች እና በርካታ የሃማስ ቢሮዎች ያሉበት ትልቅ ህንጻ ወድሟል። የህንጻው ነዋሪዎችና በአካባቢው የሚኖሩ ሰዎች ድብደባው ከመካሄዱ በፊት ለቀው እንዲወጡ ማስጠንቀቂያ ተሰጦ እንደነበር ተገልጿል።

የእስራኤል ወታደራዊ ባለሥልጣናት የሮኬት መተኮሳዎች፣ የስለላ ቢሮዎችን እና የሃማስ መሪዎች መኖሪያዎችን ዒላማ ያደረገ መሆኑን በገለጹት ጥቃት፣ የጋዛ የጤና ባለሥልጣናት እንዳሉት ሠላሳ አምስት ሰዎች ተገድለዋል። ከመካከላቸው አስሩ ልጆች መሆናቸውን እና ሁለት መቶ ሰዎች መቁሰላቸውን አክለው አመልክተዋል።

በሌላ በኩል ሃማስ በተኮሳቸው ሮኬቶች አምስት እስራኤላውያን መገደላቸው ታውቋል።

ሃማስ ካለፈው ሰኞ ጀምሮ ወደቲላቪቭ እና አካባቢዋ በመቶዎች የተቆጠሩ ሮኪቶች ተኩሷል። ትናንትም ህንጻውን ያወደመውን የአየር ጥቃት ለመበቀል ቢያንስ 130 ሮኬቶችን ተኩሷል።

የዋይት ሃውስ ቃል አቀባይ ጄን ሳኪ ትናንት በሰጡት ቃል ዩናይትድ ስቴትስ የሃማስ ቡድን እና ሌሎችም ቡድኖችን የሮኬት ጥቃቶች እንደምታወግዝ ገልፀዋል። ፕሬዚደንት ጆ ባይደን ለእስራኤል ጸጥታ እና ራሷን እና ህዝቧን ከጥቃት ለመከላከል ህጋዊ መብቷ የማይናወጥ ድጋፍ ያላቸው መሆኑም ጄን ሳኪ አክለው አስገንዝበዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታ ምክር ቤት በግጭቱ ዙሪያ ለመነጋገር ዛሬ በዝግ አስቸኳይ ስብሰባ እንደሚያደርግ ታውቋል።

XS
SM
MD
LG