ዋሺንግተን ዲሲ —
ዩናይትድ ስቴትስ በፀረ ኮቪድ-19 ትግሏ የተሻለ ምዕራፍ ላይ መድረሷን አንድ ከፍተኛ የዋይት ኃውስ ባለሥልጣን አስታወቁ።
የዋይት ሃውስ የኮሮናቫይረስ ምላሽ አስተባባሪ ጄፍሪ ዜንትስ ትናንት ዕሁድ ለሲኤንኤን በሰጡት ቃል በየቀኑ የሚከተቡ ሰዎች ቁጥር ባለፈው ወር ከነበረው ከፍተኛ ቁጥር በአርባ ከመቶ ቀንሶ ወደ ሁለት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ያቆለቆለ ቢሆንም ለአሜሪካውያን በሙሉ የሚበቃ የኮቪድ-19 ክትባት አለን ብለዋል። ዕድሜያቸው ከአስራ ስምንት ዓመት በላይ ከሆኑት አሜሪካውያን ውስጥ ሃምሳ ስምንት ከመቶው ማለትም አንድ መቶ አርባ ዘጠኝ ሚሊዮን ገደማው በሁለት ጊዜ ከሚሰጡት ክትባቶች ቢያንስ የመጀመሪያውን ተከትበዋል ብለዋል።
ይህ አሃዝ ለፕሬዚደንት ጆ ባይደን እአአ ሃምሌ 4(ጁላይ ፎር) ከሚከበረው የነጻነት በዓል በፊት ሰባ ከመቶው የሀገሪቱ ህዝብ እንደሚከተብ ተስፋ ሰጥቷቸዋል።
ሃገራችን ወደተሻለ ሁኒታ እየተጓዘች ወደተለመደው የኑሮ እንቅስቃሴም እየቃረበች ነች ያሉት የዋይት ሃውሱ ባለሥልጣን የእንቅስቃሴ ገደቦች እንደሚያሰለቹ ጭንብል መልበስ እንደሚያታክት አውቃለሁ። ነገር ግን ያልተከተባችሁ ተከተቡ፤ ሰው በሚበዛበት ቦታ በማስክ በመጠቀም ነቅተን ቫይረሱን መከላከላችንን እንቀጥል ሲሉ ተማጽነዋል።