በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የቻድ መሪ የመጀመሪያ የውጭ ሀገር ጉብኝት


የቻድ መሪ ጀነራል ማሃማት ኢድሪስ ዴቢ በኒጀር
የቻድ መሪ ጀነራል ማሃማት ኢድሪስ ዴቢ በኒጀር

አዲሱ የቻድ መሪ ጀነራል ማሃማት ኢድሪስ ዴቢ ዛሬ ወደኒጀር ተጉዘዋል። ጀነራሉ ባለፈው ወር የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት የነበሩት አባታቸው ኢድሪስ ዴቢን ህልፈት ተከትሎ የጦር ኃይሉ አመራሩን እንዲይዙ ከሰየማቸው ወዲህ ዓለም አቀፍ ጉዞ ሲያደርጉ የዛሬው የመጀመሪያ ጊዜያቸው ነው።

የቻዱ መሪ ኒጀር ዋና ከተማ ኒያሜ ሲገቡ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኡሙዱ ማሃማዱ እና ሌሎችም ከፍተኛ ባለሥልጣናት ተቀብለዋቸዋል። የቻዱ ርዕሰ ብሄር ከአዲሱ የኒጀር ፕሬዚደንት መሃመድ ባዙም ጋር ተገናኝተው እንደሚነጋገሩ ይጠበቃል።

ባለፉት ሁለት ዓመታት የጽንፈኞች ጥቃት እየተባባሰ በመጣበት ከቦርኪና ፋሶ ጋር በሚያዋስናት ድንበር አቅራቢያ በሚገኘው የምዕራብ ኒጀር አካባቢ 1200 የቻድ ወታደሮች ሰፍረዋል።

ቻድ እና ኒጀር የአምስቱ የሳህል ሃገሮች ቡድን ተብሎ የሚጠራው እና ቦርኪና ፋሶ፣ ማሊ እና ሞሪታንያን የሚያካትተው ክልላዊ ጸረ ሽብርተኛ ሰራዊት አባላት ናቸው።

ለረጅም ዓመታት ሥልጣን ላይ የቆዩትን ፕሬዚደንት ዴቢ በመግደል አዲሱ የቻድ መንግሥት ተጠያቂ ያደረገው ታጣቂ ቡድን አንዳንድ አባላት ድንበር አቋርጠው ወደኒጀር ገብተዋል እያለ ነው።

የፕሬዚደንቱ ልጅ የአሁኑ ርዕሰ ብሄር ዴቢ ሥልጣን ሊወርሱ አይገባም ብለው ተቃዋሚ ቡድኖች ድምጽ ማሰማታቸው ባይቀርም እርሳቸው ግን ሥልጣኑን ተረክበው ሥራቸውን ቀጥለዋል።

በቻድ ህገ መንግሥት መሰረት ርዕሰ ብሄርነቱን መያዝ የነበረባቸው የምክር ቤቱ ፕሬዚደንት ናቸው። ሆኖም ከዚያ ወዲህ በጦር ሰራዊቱ በሚመራው ጊዜያዊ መንግሥቱ ውስጥ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የፍትህ ሚኒስትር ቦታውን ጨመሮ በርካታ ታዋቂ ተቃዋሚ የፖለቲካ ሰዎች ተሹመዋል።

XS
SM
MD
LG