በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኮቪድ-19 በህንድ


ኮቪድ-19 በህንድ
ኮቪድ-19 በህንድ

ህንዱ ውስጥ ዕለታዊ የኮሮናቫይረስ ተያዦች ቁጥር ካለፉት ቀናት በጥቂቱ የቀነሰ ቢሆንም አሁንም እጅግ ከፍተኛ መሆኑ ታውቋል። ባለፈው የሃያ አራት ሰዓት ጊዜ 366,161 የቫይረሱ አዲስ ተያዦች እና 3,754 በሽታው ሳቢያ ለህልፈት የተዳረጉ ሰዎች መመዝገባቸውን የሃገሪቱ የጤና ባለሥልጣናት ገልፀዋል።

የህዝብ ጤና ጥበቃ አዋቂዎች ግን የቫይረሱ ተጋላጮችም ሆነ የሞቱት ሰዎች ቁጥር በባለሥልጣናቱ ከተገለጸው ይበልጣል ብለው እንደሚያምኑ እየተናገሩ ነው።

በዩናይትድ ስቴትሱ የጃንስ ሃፕኪንስ ዩኒቨርስቲ የዓለም አቀፉ ኮቪድ-19 መረጃ አጠናቃሪ ማዕከል መሰረት ህንድ ውስጥ እስካሁን በይፋ የተመዘገበው የቫይረሱ ተያዦች ቁጥር 22 ነጥብ 6 ሚሊዮን ገብቷል።

በዓለም በጠቅላላ ከተመዘገቡት 158 ነጥብ 3 ሚሊዮን የኮሮናቫይረስ ተያዦች ውስጥ ከፍተኛውን ቁጥር በያዘችው በዩናይትድ ስቴትስ 32 ነጥብ 7 ሚሊዮን ማለፉን መረጃው ጠቁሟል።

ህንድ ውስጥ መጀመሪያ የተከሰተው በከባድ ፍጥነት ተዛማቹ የኮሮናቫይረስ ዝርያ ባንግላዴሽ፣ ፈረንሳይ፣ ታይላንድ እና ብሪታንያ እንዲሁም በዩናይትድ ስቴትሷ ከኔክቲከት ክፍለ ሀገር ውስጥ መገኘቱ ተገልጿል።

ህንድ ውስጥ ከወረርሺኙ በተያያዘ ሌላም ስጋት ተፈጥሯል። የኮቪድ-19 ህሙማንን እና ከበሽታው ያገገሙ ሰዎችን የሚያጠቃ በሽታ በእጅጉ እያሳሰበ መሆኑ ታውቋል።

“ሙኮርማይኮሲስ” የተባለ በፈንገስ ወይም በሻጋታ የሚከሰት በሻታ ፊትን ሊያበላሽ በተባባሰም ዓይንን እስከማጥፋት ሊያደርስ እንደሚችል ተገልጿል። በተለይ የስኳር በሽታ ተጠቂ የሆኑ የኮቪድ-19 ህሙማን የበለጠ ተጋላጭ እንደሆኑ የጤና አዋቂዎች ያሳስባሉ።

በሌላ ዜና ፖርቱጋል ውስጥ የተሰበሰቡት የአውሮፓ ህብረት መሪዎች ፋይዘር እና ባዩንቴክ እአአ እስከ 2023 በሚኖረው ጊዜ ውስጥ ተጨማሪ 1 ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ክትባቶች እንዲያቀርቡ የቀደመው ውል እንዲታደስ ፈቅደዋል። ፋይዘር እስካሁን በነበረው ውል መሰረት ለህብረቱ አባል ሃገሮች ስድስት መቶ ሚሊዮን ክትባት አቅርቧል።

ዩናይትድ ስቴትስ በአውሮፓ ህብረቱ መሪዎች ጉባዔ ላይ ነቀፋ ቀርቦባታል። የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ጆ ባይደን ለደሆች ሃገሮች የኮቪድ-19 ክትባቶች የተሻለ ተደራሽነት እንዲኖራቸው በማለት የኮቪድ-19 ክትባቶች የፈጠራ ባለቤትነት ገደቦች በጊዜያዊነት እንዲሰረዙ ባለፈው ሳምንት ባልተጠበቀ ሁናቴ ድጋፋቸውን ሰጥተዋል።

የአውሮፓ ህብረት ምክር ቤት ፕሬዚደንት ሻርል ሚሼል ይህ አሁን ያለውን ችግር የሚያስወግድ ዓይነተኛ መፍትሄ ነው ብለን አናምንም ብለዋል። አስከትለውም ይልቁንም ዐለም አቀፉን ወረርሲኝ ለመዋጋት የሚረዳው ዩናይትድ ስቴትስ ክትባቶችን ጠቀም አድርጋ ብትልክ ነው ነው ሲሉ እሳቸውና ሊሎችም የአህጉራዊው ህብረት መሪዎች አሳስበዋል።

XS
SM
MD
LG