በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በአፍሪካ ልውጥ የኮሮናቫይረስ ዝርያዎች ወረርሽኝ ሊያገረሽ ይችላል


በደቡብ አፍሪካ ሰዎች የትራንስፖርት አገልግሎት ለማግኘት ሲጠብቁ
በደቡብ አፍሪካ ሰዎች የትራንስፖርት አገልግሎት ለማግኘት ሲጠብቁ

በአፍሪካ ለኮሮናቫይረስ የሚሰጠው ህይወት አዳኝ ክትባት ስርጭት በጣም አነስተኛ በመሆኑና አዳዲስ የቫይረሱ ዝርያዎች በስፋት እየተሰራጩ መሆኑን ተከትሎ የአፍሪካ ሀገራት የአዲስ ልውጥ ቫይረስ ወረርሽኝ ያሰጋቸዋል ሲል የዓለም ጤና ድርጅት አስታወቋል።

በአፍሪካ ልውጥ የኮሮና ቫይረስ ዝርያዎች ወረርሽኝ ሊያገረሽ ይችላል
please wait

No media source currently available

0:00 0:03:27 0:00

በአፍሪካ አዳዲስ የኮሮናቫይረስ ተጠቂዎች ቁጥር ከ4.5 ሚሊዮን በላይ የደረሰ ሲሆን 123 ሺህ ሞቶች ተመዝግበዋል። ይህም በአህጉሪቱ ያለው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ላለፉት ስድስት ሳምንታት በከፍተኛ ሁኔታ ላይ መድረሱን ያመለክታል ሲል የዓለም ጤና ድርጅት ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል።

ሆኖም ከሌሎች አህጉራት ጋር ሲነፃፀር ዝቅተኛ የሆነው አዲስ የቫይረሱ ተያዦች ቁጥር፣ በህዝቡ ዘንድ ቸልተኝነት እንዲፈጠርና የፊት መሸፈኛ ጭንብሎችን መጠቀምና ርቀትን መጠበቅ የመሳሰሉ ራስን ከቫይረሱ መከላከያ መንገዶች እንዳይተገበር እንዳደረገው የተባበሩት መንግስታት የጤና ድርጅቱ ሪፖርት ያስረዳል።

የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ዳይሬክተር የሆኑት ማቲሺድሶ ሞይቲ እንዳስታወቁት ለቫይረሱ ስርጭት እና በየጊዜው ማንሰራራት ዋናው ምክንያት የክትባቱ መዘግየትና አቅርቦቱ እጅግ አናሳ መሆን ነው።

"በኮቪድ 19 ክትባት ስርጭት የአፍሪካ ሀገራት ከዓለም እጅግ ወደ ኋላ እየቀሩ ነው። በአለም ዙሪያ ከተሰራጨው ክትባት አንድ ከመቶ የሚሆነው ብቻ ነው አፍሪካ ውስጥ የተሰጠው። ይህ ከሳምንታት በፊት ከነበረው ሁለት በመቶ የወረደ ነው። ወደ አፍሪካ ከተላከው 37 ሚሊዮን ጠብታ ክትባት ውስጥ እስካሁን ግማሽ የሚሆነው ብቻ ነው ለሰዎች የተሰጠው።"

ኪቪድ 19 ወረርሽኝ በኮሮናቫይረስ ምክንያት የሚመጣ በሽታ ነው። ሞይቲ እንደሚሉትም የአፍሪካ ሀገራት ፈጠን ብለው ቢያንስ በእጃቸው ያለውን ክትባት ወደ ሰዎች እንዲደርስ የራሳቸውን ጥረት ማድረግ አለባቸው።

የኮቪድ 19 ክትባት በፍትሃዊነት እንዲሰራጭ የዓለም ጤና ድርጅት የመሰረተው ኮቫክስ የተሰኘ ፕሮግራም እስካሁን 80 ሚሊዮን ክትባቶችን ለአፍሪካ አድርሷል። ሆኖም የኮቫክስ ባለስልጣናት እንደሚሉት ከሚመረትበት ህንድ የሚሰራጨው ክትባት ከመጋቢት ወር ጀምሮ በህንድ በከፍተኛ ሁኔታ ባንሰራራው የቫይረሱ ወረርሽኝ ምክንያት ተግዳሮት ገጥሞታል። ህንድ የምታመርታቸውን ክትባቶች ዜጎቿን ለመከተብ እየተጠቀመችባቸው በመሆኑም ለሌሎች ሀገራት የሚሰራጨው ክትባት በ140 ሚሊዮን ቀንሷል።

የዓለም ንግድ ድርጅት ለፈጠራ መብቶች የሚሰጠውን ከለላ በማንሳት ኮቪድ 19 ክትባት በስፋት መመረት እንዲጀምር የሚደረገውን ጥረት ደቡብ አፍሪካና ህንድ በዋናነት እየመሩት ይገኛሉ። ይህንን ጥረት ዩናይትድ ስቴትስ መደገፏ ደግሞ ትልቅ ነገር እንደሆነ ሞቲ ይገልፃሉ።

"ዩናይትድ ስቴትስ ለኮቪድ 19 ክትባትና ህክምናዎች የፈጠራ መብት ከለላ በጊዜያዊነት እንዲነሳ የሚደረገውን ጥረት በመደገፏ ማመስገን እፈልጋለሁ። ይህ አፍሪካ በሚሊዮን የሚቆጠር ክትባት እንድታገኝና በርካት ህይወት እንዲድን በማድረግ ትልቅ ለውጥ ያመጣል።"

በዚህ ዙሪያ የሚደረጉት ድርድሮች ቶሎ መጠናቀቃቸው ለደህነንት አስፈላጊ የሆኑት ህይወት አድን ክትባቶች ቶሎ መመረት እንዲጀምሩ ይረዳል የላሉ ሞቲ። አክለውም እስከዛው ግን ህይወት ለማዳን የሚቻልበት ፈጣኑና እርግጠኛው መንገድ እጅግ ብዙ የተከማቸ ክትባት ያላቸው ሀገራት በችግር ላይ ላሉት በማካፈል መሆኑን ያሰምሩበታል።

XS
SM
MD
LG