በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የጄፍሪ ፌልትማን የአፍሪካ ጉዞ


የዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ አምባሳደር ጄፍሪ ፌልትማን

የዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ አምባሳደር ጄፍሪ ፌልትማን ትናንት በአስመራ ከኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋራ ተነጋግረዋል።

የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረ መስቀል በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ ፕሬዚዳንት ኢሳያስና የዩናይትድ ስቴትስ ልዩ ልዑኩ ትናንት ከቀትር በኋላ አራት ሰዓት የፈጀ ውይይት እንዳካሄዱ ገልጸዋል።

ፕሬዚዳንት ኢሳያስ የአፍሪካ ቀንድ ችግሮች ለመፍታት በሚደረጉ ጥረቶች ኤርትራ ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆኗን ለዩናይትድ ስቴትስ ልዩ ልዑኩ ያረጋገጡላቸው መሆኑን የማስታወቂያ ሚኒስትሩ አክለው ገልጸዋል።

አምባሳደር ፌልትማን በበኩላቸው ዩናይትድ ስቴትስ በአፍሪካ ቀንድ ባሉ አበይት ችግሮች ዙሪያ የዩናይትድ ስቴትስ አስተዳደር ያለውን አመለካከት ያብራሩ መሆኑን የአቶ የማነ ገብረ መስቀል የትዊተር ጽሁፍ አመልክቷል።

አምባሳደር ጄፍሪ ፌልትማን ረቡዕ በካይሮ ከግብጹ ፕሬዚዳንት አብደልፋታህ ኤል ሲሲ እና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሳሜህ ሹክሪ ጋር ተገናኝተው መነጋገራቸውን ዘገባዎች አመልክተዋል።

ልዩ ልዑኩ ዛሬ ወደሱዳን ያመሩ ሲሆን የፊታችን ዕሁድ ደግሞ ወደአዲስ አበባ እንደሚጓዙ ከዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ አመልክቷል።

XS
SM
MD
LG