በዓለም ዙሪያ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በተከታታይ ለዘጠነኛ ሳምንት፣ በበሽታው ሳቢያ ለህልፈት የተዳረጉት ሰዎች ቁጥር ደግሞ ለስድተኛ ሳምንት ማሻቀቡን መቀጠሉን የዓለም የጤና ድርጅት አስታወቀ።
የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ቴድሮስ አደሃኖም ይህን የተናገሩት ትናንት በአባል ሃገራቱ የመረጃ ልውውጥ ጉባኤ ላይ ነው።
ባለፉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ የተመዘገበው የኮሮናቫይረስ ተያዦች ቁጥር በወረርሽኙ የመጀመሪያ ስድስት ወር ውስጥ ከተመዘገቡት እንደሚበልጥ የተናገሩት ዶ/ር ቴድሮስ በመሆኑም ወቅቱ የቫይረሱ ስርጭት እየቀነሰላቸው ባሉት ሃገሮችም ጭምር ከመጠንቀቅ ወደኋላ የሚባልበት አይደለም ሲሉ አሳስበዋል።
ኮቪድ-19 ህንድን በከበደ ሁኔታ ማጥቃቱን የቀጠለ ሲሆን የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኔራንድራ ሞዲ የቫይረሱን ግስጋሴ ለመቆጣጠር እንደገና የእንቅስቃሴ ክልከላዎች እንዲያውጁ ግፊቱ በርትቶባቸዋል።
ወደህንድ የተጓዙ አውስትራሊያውያን ወደ ሀገራቸው የመግባት ፈቃድ ተሰጣቸው
ወደህንድ የተጓዙ አውስትራሊያውያን ወደሃገራቸው እንዳይመለሱ ክልከላ ተደርጎባቸው መሰንበታቸው ሲታወስ ከሚቀጥለው ሳምንት ቅዳሜ ጀምረው ለመመለስ እንደሚፈቀድላቸው አውስትራሊያ አስታወቀች።
የአውስትራሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ስካት ሞሪሰን በሰጡት ቃል ለቫይረሱ የተጋለጡ ተጓዦች ግን ከህንድ አውስራልያውንን ወደሃገራቸው በሚመልሱ በረራዎች እንዲሳፈሩ እንደማይፈቀድ አስታውቀዋል።
በዓለም ዙሪያ እስካሁን በኮቪድ-19 ምክንያት ህይወታቸውን ያጡት ሰዎች ቁጥር ከ3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ማለፉን ከፍተኛውን አሃዝ በያዘችው በዩናይትድ ስቴትስ በበሽታው ሳቢያ የሞቱት ሰዎች ቁጥር ከ580 ሽህ እንዳለፈ የጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ መረጃ ማዕከል አሃዝ ያመለክታል።