በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በትራምፕ ላይ የተወሰነው ውሳኔ የመሪዎች ፌስቡክ አጠቃቀም ህግ እንዲሻሻል ሊያደርግ ይችላል


በትራምፕ ላይ የተወሰነው ውሳኔ የመሪዎች ፌስቡክ አጠቃቀም ህግ እንዲሻሻል ሊያደርግ ይችላል
please wait

No media source currently available

0:00 0:05:04 0:00

በቅርቡ በፌስቡክና በቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ላይ የተወሰነው ውሳኔ ሌሎች የዓለም መሪዎችም የማህበራዊ ትስስር ገፆችን ለመጠቀም፣ በሂደት እየወጡ ባሉ ህጎች መመራት እንዳለባቸው የሚያመላክት ሆኗል።

ፌስቡክን በበላይነት የሚቆጣጠሩትና በከፊል ገለልተኛ የሆኑት የቦርድ አባላት በፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ላይ ያሳለፉት ውሳኔ ፌስቡክን ለሚጠቀሙ የዓለም መሪዎችና ሌሎች ከፍተኛ ሀላፊነት ላይ ያሉ ሰዎችም መልዕክት የሚያስተላልፍ መሆኑን የፌስቡክ ቦርድ ቃል አቀባይ የሆኑት ዴክስ ሀንተር ቶሪክ ይናገራሉ።

"ሁሉም የፌስቡክ ተጠቃሚዎች ላይ ተፈፃሚ የሆነው ህግ ተፅእኖ ፈጣሪ የሆኑ ሰዎች ላይም ተፈፃሚ ይሆናል። ተፅእኖ ፈጣሪዎች በሌላ የተለየ ህግ መታየት የለባቸውም።"

ሆኖም በፕሬዝዳንት ትራምፕ ላይ የተላለፈው ውሳኔ እነዚህ ህጎች ምንድን ናቸው? መልዕክታቸውን በፌስቡክ ማስተላለፍ ለሚፈልጉ መሪዎችስ ምን ትርጉም ይሰጣል? የሚል ጥያቄ አጭሯል። ቴክኖሎጂ በበይነ መረብ አማካኝነት የሚደረግ የመናገር ነፃነት ላይ ያለውን ሀይልም በክፉ አይን እንዲታይ አድርጓል።

ከጋዜጠኞች፣ የመብት አቀንቃኞችና ጠበቆች የተዋቀረው የፌስቡክ ቦርድ በዚህ ሳምንት እንዳስታወቀው ባሳለፍነው ጥር ላይ በዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት ላይ ጥቃት መድረሱን ተከትሎ ግዙፉ የማህበራዊ ትስስር ሚዲያ የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕን ገፅ ማገዱ ትክክለኛ ውሳኔ ነበር ብሏል።

ቦርዱ በተጨማሪ በቀጣይ የትራምፕን ገፅ እጣ ፈንታ ለመወሰን የስድስት ወር ጊዜ የሰጠ ሲሆን ፌስቡክ የቦርዱን ውሳኔ በጥንቃቄ እንደሚያጠናው ተናግሯል።

የዲሞክራሲና ቴክኖሎጂ ማዕከል ዲሬክተር የሆኑት ኤማ ላውንሶ በጉዳዩ ላይ እንዲህ ይላሉ።

"ፌስቡክ ትራምፕን የማገድ ውሳኔውን ለበላይነት ለሚቆጣጠረው ቦርድ ሊተውለት የፈለገ ይመስላል። ቦርዱ ደግሞ መልሶ ለፌስቡክ 'አይ ይህ የእናንተ ችግር ነው። ፖሊሲያችሁን በግልፅ አስቀምጡና እነዛን ፖሊሲዎች ይፃረራል ወይም አይፃረርም ብላችሁ ውሳኔአችሁን ሱጡ' ብሎ መልሶላቸዋል።"

ላውንሶ እንደሚሉት ቦርዱ በመናገር ነፃነትና ሰዎችን ከጥቃት በመጠበቅ መሀል ውስብስብ በሆነው ጉዳይ ላይ ብዙ ታግሏል።

"ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ህግ ለሰዎች የመናገር ነፃነት መብት ጥበቃ ያደርጋል። ነገር ግን አንዳንድ ንግግሮች ደግሞ ዓለምን ለሁከትና ብጥብጥ እንደሚዳርጉም ይታወቃል።"

የፌስቡክ ቦርድ ያሳለፈው ውሳኔ በዩናይትድ ስቴትስ ህግ አውጪዎች መሃል የተደበላለቀ ስሜት ፈጥሯል። ወግ አጥባቂዎቹ ትራምፕ ከፌስቡክ ውጪ መደረጋቸውን ሲኮንኑ ሌሎች በቋሚነት ሊታገዱ ይገባ ነበር ይላሉ። ትራምፕ በውሳኔው ላይ አስተያየታቸውን ባይሰጡም፣ ረቡዕ ለት በአዲሱ ድህረ ገፃቸው አማካኝነት የቴክኖሎጂ ኩባንያዎችን ነቅፈዋል።

የዓለም መሪዎች የገፆቻቸው ላይ የሚያስተላልፏቸው መልዕክቶች ምንም ያክል አወዛጋቢ ወይም የተሳሳቱ ቢሆኑ ባላቸው የፖለቲካ አቋም ምክንያት ብቻ ተፈላጊ ዜና አድርጎ መቁጠር በዋናነት መቀየር ያለበት ጉዳይ እንደሆነ የፌስቡክ ቦርድ በዋናነት አፅንኦት ሰጥቶ መናገሩን የቦርዱ ቃል አቀባይ የሆኑት ዴክስ ሀንተር ቶሪክ ያስረዳሉ።

"ይሄ ተፈላጊ ዜና የመሆን ጉዳይ ወይም አንድ ፅሁፍ ፌስቡክ ላይ ለመቀመጡ ተፈላጊ ዜና መሆኑ ብቻ እንደምክንያት በመቅረቡ ጉዳይ ላይ እኛ እያልን ያለነው፣ ሚዛናዊነት ይኑር ከተባለ በዋናነት ቅድሚያ መሰጠት ያለበት የሰዎችን ደህንነት መጠበቅ ላይ ነው።"

በጥላቻና ፅንፈኝነትን ለማጥፋት የተቋቋመው ዓለም አቀፍ እንቅስቃሴ ፕሬዝዳንት ዌንዲ ቪያም የዓለም መሪዎች የተለየ አካሄድ መኖር የለበትም ይላሉ።

"በዓለማችን ላይ ያሉ አብዛኞቹ ፖለቲከኞች የተለዩ ህጎች አይፈልጉም ምክንያቱም አላማቸው ዲሞክራሲን ማሳነስ ወይም አንድን ማህበረሰብ መጥፎ አርጎ ማቅረብ አይደለም።"

ቪያ አክለው የፌስቡክ ቦርድ ያሳለፈው ውሳኔ ጠንካራ ህግ ለማውጣት ወደፊት አንድ እርምጃ የሚያራምድ ነው ይላሉ። በተለይ ፌስቡክ ያልዳበረ ዲሞክራሲ ባለባቸው ሀገራት ውስጥም የሚንቀሳቀስ እንደመሆኑ መጠን፣ ህጉ በጣም አስፈላጊ ነው።

"በፖሊሲያቸው ዙሪያ የተሰጡትን ምክሮች በደንብ አጢነው ሊያዩዋቸው ይገባል። የኛን ድርጅት ጨምሮ በርካት የሲቪክ ማህበራት ለረጅም ግዜ ስንናገር የነበርውም ይህንኑ ነው። ነገር ግን ሰሚ ባለማግኘታችን ሰዎች ሞተዋል፣ ዲሞክራሲ ተጎድቷል። እሴቶቻችን ብለው ባስቀመጧቸው መመሪያዎች መሰረት መስራት አለባቸው።"

አሁን ኳሱ ተንከባሎ ተመልሶ በፌስቡክ መሬት ላይ ሆኗል። የፖለቲካ አመራሮች፣ ተፅእኖ ፈጣሪዎች እና በዓለም ዙሪያ ያሉ 2.8 ቢሊዮን ተጠቃሚዎች የማህበራዊ ትስስር ሚዲያው ለውጦች ያደርግ እንደሆን ለማየት እየጠበቁ ነው።

XS
SM
MD
LG