የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በቀጣዮቹ ሁለት ወራት 70 በመቶ የሚሆኑ የሀገሪቱ አዋቂ ዜጎች ቢያንስ አንድ ጊዜ እንዲከተቡ ለማድረግ ዕቅድ ይዘዋል። ትናንት በዋይት ኃውስ ባሰሙት ንግግር ላይ ባይደን ተጨማሪ ዜጎች እንዲከተቡ ያስቀመጡትን ግብ ይፋ አድርገዋል።
“ግባችን በጎረጎሳዊያኑ አቆጣጠር ከሀምሌ 4 በፊት 70 በመቶ የሚሆኑት አዋቂ አሜሪካዊያን ቢያንስ አንድ ጊዜ እንዲከተቡ፣ 160 ሚሊየን አሜሪካዊያን ደግሞ ሙሉ ክትባት እንዲያገኙ ነው። በመጭው 60 ቀናት ወደ 100 ሚሊየን የሚጠጉ አሜሪካዊያን ለተወሰኑት ለመጀመሪያ ጊዜ ለሌሎች ደግሞ ለሁለተኛ ጊዜ ክትባት ይሰጣል ማለት ነው። ርግጥ ነው አሜሪካዊያን ከሀምሌ 4 በኋላም መከተብ ይችላሉ፣ ነገር ግን ማንም ቢሆን እስከዚያ መጠበቅ የለበትም። ከቀኑ በፊት ቢያንስ አንድ ጊዜ በመከተብ የ70 በመቶ ግባችንን ለማሳካት እንሞክር” ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ባይደን የምግብ እና መድሃኒት አስተዳደር ተቋም ከፈቀደ ዕድሜያቸው ከ12-15 ለሚሆኑ ተማሪዎች ሁለት ዙር የፋይዘር ክትባት በአስቸኳይ ለመስጠት መንግሥት ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል። ይህ ፈቃድ እስከሚቀጥለው ሳምንት ድረስ እንደሚገኝ ይጠበቃል።
በተያያዘ ዜና ፋይዘር የተሰኘው የክትባት አምራች ተቋም፣ ከ2 እስከ 11 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ህጻናትን መከተብ ይችል ዘንድ የድንገተኛ ግልጋሎት ፈቃድ ለማግኘት የምግብ እና መድሃኒት አስተዳደርን እንደሚጠይቅ በትናንትናው ዕለት አስታውቋል።
ዝርዝሩን ከተያያዘው የድምጽ ፋይል ያድምጡ፡፡