በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ተመድ በትግራይ ጉዳይ


በትግራይ ክልል በችግር ላይ ላለው ህዝብ ሰብዓዊ ረድዔት በነጻነት ተንቀሳቅሶ ለማቅረብ የሚደረገው ጥረት በሀገሪቱ ባለው ውስብስብ እና የማያስተማምን የፀጥታ ሁኔታ ምክንያት አሁንም መስተጓጎሉ እንደቀጠለ ባልደረቦቻችን ገልጸውልናል ሲል ተመድ አስታወቀ።
የተመድ ዋና ጸኃፊ ምክትል ቃል አቀባይ ፋርኻን ሃቅ በትናንት ዕለታዊ ጋዜጣዊ መግለጫቸው በክልሉ ግጭቱ ከተቀሰቀሰ ስድስት ወር በተጠጋው በዚህ ወቅት አብዛኛው የገጠሩ አካባቢ አሁንም የኮሙዩኒኬሽንና የኤሌክትሪክ አገልግሎቶች እንደሌለው ይህም የጤና አገልግሎቶች እና የውሃ አቅርቦት ሌላም አገልግሎት እንዳይደርስ አድርጓል ብለዋል።
የክልሉ ህዝብ ያለበት የምግብ ችግር አሁንም እጅግ የከበደ እንደሆነ የተናገሩት የመንግሥታቱ ድርጅት ምክትል ቃል አቀባይ ሃቅ በመላዋ ትግራይ በእኛ ግምት አራት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ህዝብ የምግብ እርዳታ የሚጠብቅ ነው ሲሉ አስረድተዋል። ድርጅታቸው ከሌሎች የሰብዓዊ ረድዔት አጋሮቹ ጋር ሆኖ ለዚህ ችግር የሚሰጠውን ድጋፍ ማሳደጉን እንደቀጠለ ገልጸው ይህም የጾታዊ ጥቃቶች ሰለባዎች መለየት እና አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግን ያካትታል ብለዋል።
የዓለም የምግብ ፕሮግራም ድርጅት ካለፈው እአአ መጋቢት ወር ወዲህ ባከፋፈለው ዘጠኝ ሽህ ቶን ምግብ በክልሉ በሰሜን ምዕራብ እና በደቡባዊ ዞን አምስት መቶ ሃያ ዘጠኝ ሽህ ነዋሪዎች ሊያደርስ መቻሉን በእዳጋ ሃሙስ እና አጺቢ ከተሞች ለሰላሳ አራት ሽህ ህዝብ የምግብ እርዳታ ማከፋፈሉን እና ባለፈው ሳምንት ከሰባት መቶ ሽህ በላይ ህዝብ ውሃ የማጓጓዝ አገልግሎት መሰጠቱን ዘርዝረዋል።
የረድዔት አጋሮቻችን እስካሁን ለሁለት መቶ ሰማኒያ አምስት ሽህ ተፈናቃዮች የመጠለያና ምግብ ያልሆኑ ቁሳቁስ እርዳታዎችን አድርሰዋል፤ ይህ ግን በእርዳታ ዕቅዳችን ካቀድነው የህዝብ ቁጥር አስር ከመቶው ብቻ ነው ሲሉ የመንግሥታቱ ድርጅት ቃል አቀባይ አመልክተዋል።
አስከትለውም መቀሌ ከተማ ውስጥ ከአስራ ዘጠኝ ሽህ በላይ ሰዎች ለማስጠለል የሚችል የተፈናቃዮች ካምፕ የማዘጋጀቱ ሥራ እንደቀጠለ ተናግረዋል።
ህዝቡ ካለበት ችግር አንጻር እየተሰጠ ያለው የእርዳታ ምላሽ እጅግ አናሳ መሆኑ የሰብዓዊ ረድዔት አጋሮቻችን አስታወቀውናል በሚፈለገው መጠን እርዳታ ለማቅረብ ገንዘብ እና ባልተገደበ እና የደህንነት ጥበቃ ባልተለየው መልኩ ተረጂው ህዝብ ጋር መድረስ መቻል ይኖርብናል ብለዋል።

XS
SM
MD
LG