የኮቪድ-19 ወረርሺኝ ለሁለተኛ ጊዜ በከበደ ሁኔታ እየተዛመተ ላለባት ለህንድ የተላኩ አንገብጋቢ የህክምና አቅርቦቶች ዛሬ ገብተዋል።
አንድ መቶ የህሙማን መተንፈስ አጋዥ መሳሪያዎች ወይም ቪንቲሌተሮች እንዲሁም ዘጠና አምስት ከከባቢ አየር ኦክሲጂን ለይተው የሚሰበሰቡ መሳሪያዎች ጭኖ ከብሪታንያ የተነሳው አውሮፕላን ዛሬ ማክሰኞ ማለዳ ኒው ዴልሂ ገብቷል።
ሌሎችም ሃገሮች ህንድን በአጣዳፊ የሚያስፈልጋትን የህክምና ቁሳቁስ በመላክ ለመርዳት ቃል ገብተዋል። ፈረስንሳይ ቬንቲሌተሮች ኦክሲጂን ማዘጋጃ መሳሪያዎች እና የፈሳሽ ኦክሲጂን መያዣዎች እንደምትልክ አስታውቃለች።
ጀርመን እስራኤል እንዲሁም የህንድ አጎራባች እና የረጅም ጊዜ ጠበኛዋ ፓኪስታን ቫይረሱን መከላከያ ቁሳቁስ መድሃኒት እና መመርመሪያ አቅርቦቶች እና ቬንቲሌተሮች እንዲሁም ኦኮሲጂን እንደሚልኩ አስታውቀዋል።
በህንድ የብሪታንያ ከፍተኛ ኮሚሽን እንዳስታወቀው በጠቅላላው በዚህ ሳምንት ዘጠኝ አውሮፖላኖቻን አንገብጋቢ የሆኑ የህክምና አቅርቦቶችን እና መሳሪያዎችን ጭነው ህንድ ያደርሳሉ ብሏል።
የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም የህንድን የወረሺኙን ይዞታ እጅግ አሳዛኝ ብሎ ከመግለጽም በላይ ነው ብለዋል። በሽዎች የሚቆጠሩ ኦክሲጂን ከከባቢ አየር አውጥተው የሚሰበስቡ መሳሪያዎች፤ ተንቀሳቃሽ የመስክ ሆስፒታሎች እና የላቦራቶሪ አቅርቦቶችን በመላክ የተቻለንን ሁሉ በማድረግ ላይ ነን ሲሉም አክለዋል።
ድርጅታቸው ተጨማሪ 2600 ሰራተኞችን ወደህንድ እንደሚልክም አስታውቀዋል።
ህንድ ዛሬ 322,144 አዲስ የቫይረሱ ተያዦች የመዘገበች ሲሆን በተከታታይ በየቀኑ ከ300,000 በላይ ሲመዘገቡ ዛሬ ስድስተኛ ቀን መሆኑ ነው።