በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የጸጥታ ምክር ቤት ኢትዮጵያ ውስጥ መረጋጋት እንዲመለስ አሳሰበ


ትግራይ ክልል ውስጥ የሰብዓዊ ረድዔት በተፋጠነ ሁኔታ የሚዳረስበት ሁኔታ እንዲጠናከር እና ክልሉ ወደ ነበረበት መረጋጋት እንዲመለስ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት አሳስቧል። በሌላ በኩል ክልሉ ውስጥ ተፈጥረዋል ለሚባሉት የመብቶች ጥሰቶችና በደሎች አጥፊዎችን በተጠያቂነት ለመያዝ መንግሥት ቁርጠኛ መሆኑን በመንግሥታቱ ድርጅት የኢትዮጵያ ልዑክ ያሳወቀ ሲሆን ኢትዮጵያ ውስጥ ህግን የማስከበር ተግባር የኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ መሆኑን አመልክቷል።

15 ሀገራትን የሚያቅፈው የጸጥታ ምክር ቤት፣ በትግራይ ክልል በሴቶችና በልጃገረዶች ላይ ይፈጸማል ስለሚሉት ዘገባዎች “ጽኑ ስጋት” እንዳለው ገልጿል። በጉዳዩ ላይ ምርመራ እንዲደረግና ጥፋተኞቹ ተጠያቂ እንዲሆኑም ጥሪ አድርጓል። ነገር ግን በቀጥታ አላወገዘም።

የጸጥታው ምክር ቤት አባል ሀገሮች፣ አለም አቀፉ የረድኤት ጥረት፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ አስቸኳይ የሰብአዊ ረድኤት መርሆች መሰረት እንዲካሄድ ጥሪ ያደርጋል። መርሆቹም ሰበአዊነትን፣ ገለልተኛነትን፣ ወገንተኛነትን ባስወገደ መልክና በነጻ መስራትን ያቀፉ ናቸው። በትግራይ ያለው የጸጥታ ጉድለት፣ የሰብአዊ ረድኤት ስራን ያሰናክላል በማለት፣ ሁኔታዎች እንዲረጋጉ ጥሪ አድርጓል።

ከትግራይ እየተሰሙ ያሉት፣ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ በደሎች፣ እጅግ የሚያስደነግጡና የሚረብሹ ናቸው። በደሉ የተፈጸመባቸው ሴቶች በአብዛኛው በወታደሮች፣ በዘግናኝ ሁኔታ እንደተደፈሩ። አንዲት ሴት ላይ በህብረት ሆነው እየተፈራረቁ የወሲብ ጥቃት እንደሚፈጽሙባቸው መናገራቸውን፣ ዘገባዎች ጠቁመዋል ይላል የጸጥታው ምክር ቤት ያወጣው መግለጫ።

አንድ ከፍተኛ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለሥልጣን፣ በያዝነው ሳምንት በተናገሩት መሰረት፣ በትግራይ ክልል ውስጥ በሴቶች ላይ የሚፈጸመው የጭካኔ ተግባር መጠንና ስፋትን በሚመለከት፣ የተሟላ መረጃ ለማግኘት ብዙ ወራት ሊፈጅ ይችላል።

የጸጥታ ምክር ቤት ኢትዮጵያ ውስጥ መረጋጋት እንዲመለስ አሳሰበ
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:58 0:00

የጸጥታው ምክር ቤት አባላት፣ ቀጠናዊ የሽምግልና ጥረትን አጥብቀው እንደሚደግፉ ገልጸዋል። በተለይም የአፍሪቃ ህብረትና የምስራቅ አፍሪቃ የልማት ትብብር በይነ-መንግሥታት ኢጋድ፣ ስለጉዳይ መስራታቸውን እንዲቀጥሉ አጽኖኦት ሰትተውበታል።

በጸጥታው ምክር ቤት፣ በጉዳዩ ላይ መግባባት እንዲኖር የሚደረገውን ድርድር የመራችው አየርላንድ መሆንዋ ታውቋል። አየርላንድ ባለፈው ጥር ወር፣ በጸጥታው ምክር ቤት ለሁለት አመታት የሚዘልቅ የተረኛ አባልነት ቦታ ካገኘች ወዲህ፣ በትግራይ ጉዳይ ላይ፣ ሁለት ጊዜ ኦፊሴላዊ ያልሆኑ ስብሰባዎች ጠርታለች። ኢትዮጵያ ኦፊሴላዊ የጸጥታው ምከር ቤት አጀንዳ ስላልነበረች ነው፣ ኦፊሴላዊ ያልሆነ ስብሰባ የጠሩት።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአየርላንድ መልዕክተኛ ጀርልዲን ባይርን ኔሰን ባለፈው ረቡዕ፣ በጆርጅ ታውን ዩኒቨርሲቲ በትግራይ ጉድይ ላይ በተደረገው ስብሰባ ሲናገሩ፣ የጸጥታው ምክር ቤት፣ በትግርይ ጉድይ ላይ ያሳየው ዝምታ “ጆሮ ይደፍናል።” ዝምታውም ሁኔታውን አልረዳም ብለው ነበር።

ዛሬ ግን “የጸጥታው ምክር ቤት፣ በትግራይ ስላለው ሰብአዊ ሁኔታ ያለውን ስጋት ለመጀመርያ ጊዜ፣ በአንድ ድምጽ አሰምቷል” ሲሉ፣ ባወጡት መግለጫ ጠቅሰዋል።

የጸጥታው ምክር ቤት፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የወሰዳቸው የመጀመርያ እርምጃዎች መኖራቸውን ተቀብሎ፣ በትግራይ ያሉት የሰብአዊ ረድኤት ድርጅቶች፣ ካለምንም ገደብ ለሚያስፈልጋቸው ሁሉ ረድኤት ለማቅረብ እንዲችሉ ጥሪ አቅርቧል።

ካለፈው ጥቅምት ወር መገባደጃ አንስቶ፤ ትግራይ በግጭት ስትታመስ ቆይታለች። የኢትዮጵያ መንግስት እንደሚለው፣ ጦርነቱ የተጀመረው ህዝባዊ ወያነ ሐርነት ትግራይ፣ በቦታው የነበረውን ወታደራዊ ሰፈር ካጠቃ በሁዋላ ነው።

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ያለው የኢትዮጵያ ሚስዮን፣ የጸጥታው ምክር ቤት ላውጣው መግለጫ በትዊተር ምላሽ ሰጥቷል።

“ኢትዮጵያ ያለው የህግ ማስከበር እንቅስቃሴ፣ የሰብአዊ መብቶች ህጎችን ባቀፉት፣ የሀገሪቱ ህጎች ላይ የተመሰረተ የአገር ውስጥ ጉዳይ መሆኑን፣ ሚስዮኑ ሊያሰምርበት ይፈልጋል። በትግራይ ህግና ሰርአት ለማስከበር የተወሰደው እርምጃ፣ በሀገሪቱ የሉአላዊነት ደንብ መሰረት ነው” ይላል፣ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ያለው የኢትዮጵይ ሚስዮን፣ በትዊተር ያወጣው መግለጫ።

የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ፣ የወሲብ ጥቃቶችን ባካተቱ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ላይ፣ ምርምራ አካሄዳለሁ ተጠያቂነት እንዲኖርም አደርጋለሁ ማለቱ የሚታወቅ ነው። ሰብአዊ ረድኤት እያደረገ መሆኑንም ገልጾ፣ በትግራይና ከዚያም አልፎ የሚያስፈልገውን ረድኤት ለማሟላት፣ አለም አቀፍ ማህበረሰብ የረድኤት ጥረቱን እንዲያፍጥን ጥሪ አድርጓል።

የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር፣ 4.5 ሚልዮን የሚሆኑ፣ ወደ 6 ሚልዮን የሚጠጉ ሰዎች ማለት ነው፣ ሰብአዊ ረድኤት ያስፈልጋቸዋል ብሏል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ በያዝነው አመት፣ በትግራይና በተቀረው የኢትዮጵያ ዙርያ፣ 16 ሚልዮን የሚሆኑ ስዎችን ለመርዳት፣ $1.5 ቢልዮን ዶላር እንደሚያስፈልገው አስታውቋል።

XS
SM
MD
LG