በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የኮቪድ-19 ክትባት በዓለም


ዩናይትድ ስቴትስ ከጠቅላላው በአዋቂ ዕድሜ ክልል ውስጥ ካሉ አሜሪካውያን ግማሹ ቢያንስ የመጀመሪያውን የኮቪድ-19 ክትባታቸውን እንደወሰዱ ገለጸች። ህንድ ደግሞ ከጠቅላላው ህዝቧ አንድ ከመቶውም አልተከተበም።

ዛሬ የህንድ የጤና ሚኒስቴር በሰጠው መግለጫ እንዳስታወቀው ባለፈው የሃያ አራት ሰዓት ጊዜ ውስጥ 273,810 አዲስ የኮሮናቫይረስ ተጋላጮች መገኘታቸውን አስታወቀ። እስካሁን በአንድ ቀን ብቻ ከተገኙ የቫይረሱ ተያዦች ቁጥር የዛሬው ከፍተኛው መሆኑንም የሚኒስቴሩ መግለጫ አስታውቋል።

በህንዱዋ ዋና ከተማ ኒውዴሊ ባለፉት ቅርብ ቀናት የኮሮናቫይረስ ምርመራ ሲደረግ ከሦስት ሰዎች አንዱ ላይ ቫይረሱ እንደተገኘ የከተማዋ የጤና ሚኒስተር ተጠሪ አስታውቋል።

“ቁጥሩ በፍጥነት እየጨመረ ነው፣ የሆስፒታል አልጋዎችም እየሞሉ ነው” ሲሉ ባልሥልጣኑ ስጋታቸውን ገልጸዋል። የከተማዋ ነዋሪዎች በሆስፒታሎች ስላለው የኦክሲጂን፥ የህሙማን አልጋና መድሃኒት እጥረት በማህበራዊ መገናኛዎች ላይ ቅሬታቸውን እያሰሙ መሆናቸው ታውቋል።

ህንድ ውስጥ ያለው አጠቃላዩ የኮሮናቫይረስ ተጋላጭ ቁጥር ከአስራ አምስት ሚሊዮን ያለፈ ሲሆን በአሃዙ ብዛት ሰላሳ አንድ ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ተያዦች ካሏት ከዩናይትድ ስቴትስ ቀጥላ ከፍተኛውን ቁጥር እንደያዘች ናት።

በክትባት ረገድ ደግሞ እስካሁን የቫይረሱን መከላከያ የተከተበው ህዝቧ ቁጥር ከአጠቃላዩ ከአንድ ከመቶ በጥቂቱ ከፍ የሚለው ብቻ መሆኑን የዓለምን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ይዞታ የሚያጠናቅረው የዩናይትድ ስቴትስ የጃንስ ሃፕኪንስ ዩኒቨርስቲዎ የመረጃ ማዕከል አመልክቷል።

በኮቪድ-19 ሳቢያ ትናንት ዕሁድ በአንድ ቀን ከፍተኛውን ለህልፈት የተዳረጉ ሰዎች ቁጥር እንደመዘገበች የተናገረችው ኢራን አራት መቶ አምስት ሰዎች መሞታቸውን አስታወቀች። ትናንት ብቻ በቫይረሱ መያዛቸው በምርመራ የተረጋገጠ ሃያ አንድ ሽህ ሰዎች መገኘታቸውንም የኢራን የጤና ሚኒስቲር አስታውቋል።

ኢራን ከአካባቢው ካሉት ወረርሺኙ የጸናባቸው ሃገሮች አንዷ ብትሆንም በኢኮኖሚው ላይ ጉዳት ያስከትላል በማለት የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት እንቅስቃሴዎችን ለተራዘመ ጊዜ ማገድ አይቻለኝም ብላለች።

በጆንስ ሆፕኪንስ መረጃ መሰረት የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት እንቅስቃሴዋ አዝጋሚ እና የምትጠቀመው በተለያዩ በሃገር ውስጥ የተመረቱ ክትባቶች ሲሆን እስካሁን በተሟላ መልኩ የተከተበው ሰው ከህዝቧ ከአንድ ከመቶ እጅግ ያነሰው መሆኑ ታውቋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ እስራኤል ከዝግ ስፍራዎች በስተቀር ውጭ ላይ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ መጠቀምን ግዴታ የሚያደርገውን ደንብ አንስታለች። የሃምሳ ስድስት ከመቶው ህዝቧ ክትባቱን መውሰዱን የሆፕኪንስ መረጃ ጠቁሟል።

XS
SM
MD
LG