የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን ዛሬ ሃሙስ አስቀድሞ ባልተገለጸ ጉብኝት አፍጋኒስታን ዋና ከተማ ካቡል ገብተዋል።
ብሊንከን ዩናይትድ ስቴትስ የቀሩዋትን ወታደሮች የምታስወጣ ቢሆንም ከአፍጋኒስታን ጋር ስላላት አጋርነት አሁንም ቁርጠኝነቷ እንደፀና የሚቆይ መሆኑ ለሀገሪቱ መሪዎች ገልጸውላቸዋል።
ከአፍጋኒስታን ፕሬዚዳንት አሽራፍ ጋኒ እና ከሌሎችም ባለሥልጣናት ጋር የተነጋገሩት የዩናይትድ ስቴትሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብሊንከን የሀገሮቻችን አጋርነት እየተቀየረ ነው፤ ነገር ግን ዘላቂ አጋርነት ነው ብለዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ወደአፍጋኒስታን የተጓዙት ትናንት የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ጆ ባይደን በዚያች ሃገር ያሉት የዩናይትድ ስቴትስ ወታደሮች በሙሉ እአአ 2021 መስከረም 11 በሚኖረው ጊዜ ውስጥ በሙሉ እንደሚወጡ ትናንት ይፋ ባደረጉ ማግስት ነው። የአፍጋኒስታን ፕሬዚዳንት ጋኒ በበኩላቸው "ውሳኔያቸውን እናከብራለን፤ እኛም ቅድሚያ ትኩረት የምንሰጣቸውን ጉዳዮቻችንን እናስተካክላለን" ብለዋል።
አንድ ከፍተኛ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለሥልጣን በሰጡት ቃል ዩናይትድ ስቴትስ አፍጋኒስታን ውስጥ ወታደራዊ ሃይል የማይኖራት ቢሆንም ማናቸውንም ሊከሰት የሚችል ስጋት ለመጋፈጥ ግን ዓቅሙ አላት ሲሉ አስረድተዋል።
ፕሬዚዳንት ባይደን በቴሌቭዥን ባደረጉት በትናንቱ መግለጫቸው የእፍጋኒስታኑ ጦርነት ከትውልድ ወደትውልድ እንዲቀጥል ፈጽሞ የታቀደ አልነበረም ብለዋል።