በዩናይትድ ስቴትስ የጆንሰን ኤንድ ጆንሰኑ የኮቪድ-19 ክትባት በወሰዱ ሰዎች ላይ የታየው የደም መርጋት ከክትባቱ ጋር ግንኙነት ይኖረው እንደሆን እየመረመረ ያለው የጤና ጠቢባንን ያሰባሰበው ነጻ የምክክር ኮሚቴ ስለጉዳዩ ተጨማሪ መረጃዎች እስኪያሰባስብ በሚል የመጨረሻ ውሳኔ መስጠትን አዘግይቶታል።
የዩናይትድ ስቴትስ የበሽታ መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል (ሲዲሲ) እና የምግብ እና የመድሃኒት አስተዳደር (ኤፍዲኤ) ክትባቱን በወሰዱ ስድስት ሴቶች ላይ የተከሰተውን የደም መርጋት ተከትሎ የጆንሰን ኤንድ ጆንሰኑ ክትባት መክተቡ ለጊዜው እንዲገታ ከትናንት በስቲያ ምክረ ሃሳብ አቅርቧል። ይህንኑ ተከትሎ ትናንት የጤና ባለሙያዎች ነጻ የምክክር አካል ትናንት አስቸኳይ ስብሰባ አካሂዷል።
ሲሬብራል ቬነስ ሳይነስ ትሮምቦሲስ ተብሎ የሚታውቀው የደም መርጋት ዓይነት ስድስቱ ሴቶች ክትባቱን ከወሰዱ በኋላ ከስድስት እስከ አስራ ሦስት ቀን ቆይተው የደም መርጋቱ እንደገጠማቸው እና ከመካከላቸው አንዷ ሴት ህይወታቸው እንዳለፈ ተገልጿል። በጽኑ ታመው ሆስፒታል ከሚገኙ መካከል አንዲት ሴትም እንደሚገኙ ተገልጿል።
ዕድሜያቸው ከአስራ ስምንት እስከ አርባ ስምንት ዓመት የሆኑት ሴቶች፣ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የጆንሰን ኤንድ ጆንሰኑን ክትባት ከወሰዱት ከሰባት ሚሊዮን በላይ ተከታቢዎች መሃል ስድስቱ መሆናቸው ነው።
ስለክትባቱ እና የደም መርጋቱ ጉዳይ ተጨማሪ መረጃ ማግኘት ያስፈልጋል ብለው ከተከራከሩት የአማካሪ ባለሙያዎቹ ኮሚቴ አባላት በዋሽንግተን ዩኒቨርስቲ የዓለም ጤና ኤክስፐርት ዶ/ር ቤት ቤል ናቸው፥ ሆኖም የተፈጠሩት የደም መርጋት ክስተቶች እጅግ በጣም ያልተለመዱ ወይ ያልተደጋገሙ በመሆናቸው ክትባቱ ችግር አለው የሚል መልዕክት ለኅብረተሰቡ ማስተላለፍ አልፈልግም እንዳሉ ተጠቅሷል።
በሌላም በኩል ከተከሰቱ የደም መርጋት ሁኔታዎች ጋር ግንኙነት ሊኖረው ይችላል የተባለውን ሌላኛውን የአስትራ ዜኒካውን የኮቪድ-19 ክትባት በሃገርዋ ለዘለቄታው እንዳይሰጥ በመከልከል የመጀመሪያ ሃገር ሆናለች።
በዓለም ዙሪያ በኮቪድ-19 ሳቢያ ለህልፈት የተዳረጉ ሰዎች ቁጥር ወደሦስት ሚሊዮን መቃረቡን እና በአጠቃላይ በቫይረሱ የተያዙት ሰዎች ደግሞ 138 ነጥብ 2ሚሊዮን መግባቱን የጃንስ ሃፕኪንስ ዩኒቨርስቲው የኮቪድ መረጃ ማዕከል አስታውቋል።
በብዙ ሃገሮች የቫይረሱ መዛመት እየጨመረ ሲሆን መጪውን የቶኪዮ ኦሊምፒክስ ጨምሮ የተለያዩ ዝግጅቶች በታቀደው መሰረት መከናወናቸው ላይ ጥርጣሬ እየፈጠረ መሆኑ ተመልክቷል።
የጃፓን የገዢው ሊበራል ዲሞክራቲክ ፓርቲ ዋና ጸሃፊ ቶሺሂሮ ኒካይ የቫይረሱ መዛመት ከቁጥጥር ውጪ ከሆነ ውድድሩ መሰረዝ ይኖርበታል ማለታቸው ተገልጿል።