(ዝርዝሩን ከተያያዘው ፋይል ያዳምጡ)
በዩናይትድስ ቴትስ ሲያትል ከተማ ነዋሪ የሆነችው አሜሪካዊቷ ኤልኖር አንጀሊተስ በወጣትነታቸው ከኢንዶኔዥያና ከኔዘርላድ በስደት ወደ አሜሪካ ከመጡ ወላጆቿ ነው የተወለደችው። ባለቤቷም እንዲሁ ለከፍተኛ ትምህርት ወደ አሜሪካ የመጣ ግሪካዊ ሲሆን ቺካጎ ውስጥ ተዋውቀው ከተጋቡ በኃላ ካፈሯቸው ሁለት ወንዶች ልጆች በተጨማሪ የስድስት ወር ህፃን ሆና ከኢትዮጵያ በማደጎ የወሰዷት የ12 አመት ልጅ አለቻቸው። ሌይላ አንጀሊተስ።
"ሌይላን ለመጀመሪያ ጊዜ የተዋወቅናት የ6 ወር ህፃን እያለች አዲስ አበባ ላይ ነው። እኔና ባለቤቴ አብረን ነበርን ነበር እና በጣም ደስ የሚል ስሜት ነበር። በተለይ ባለቤቴ ሁለቱ ልጆቹ ተወልደው ሲያቅፋቸውና እንኳን ደስ አለህ ሲሉት የተሰማው ስሜት ነበር የተሰማው።"
የስደተኝነትን ህይወት በየግላቸው የሚያውቁት ኤልኖርና ባለቤቷ ሌይላ ስለሀገሯ እንድታውቅ ወደ ኢትዮጵያ የወሰዷት ገና የሶስት አመት ልጅ እያለች ነበር። ይህን የመጀመሪያ ጉዞዋን ባታስታውሰውም ሌይላ ከእናቷ ጋር በተደጋጋሚ ወደ ኢትዮጵያ ያደረገቻቸውን ጉዞዎች በፅሁፍ ታሰፍር ነበር።
"መፃፍ በጣም ነው ደስ የሚለኝ። ኢትዮጵያ ሄጄ ያሳለፍኳቸውን ትዝታዎች በወረቀት ላይ ስፅፋቸውና ለሰው ሳካፍላቸው በጣም ደስ ይለኛል።"
እነዚህ ጉዞዎች ናቸው ዛሬ በርካታ የኢትዮጵያ ህፃናትን ማንበብና መፃፍ የሚያበረታቱ፣ ስነ-ምግባርን የሚያንፁና፣ በኢትዮጵያ መሰረታዊ ትምህርትን የሚያስፋፉ መፅሀፍት መነሻ የሆኑት። እናትና ልጅ 'ሰፊ ልብ፣ ትልቅ ህልም' በሚል ባቋቋሙት ድርጅት አማካኝነት በተለያዩ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች የተፃፉ የህፃናት መፅሀፎችን በነፃ እንደሚያሰራጩ ኤልኖር ትናገራለች።
"በጣም ልቤን የነካው ነገር ልጆች መፅሃፍ ማግኘት ካልቻሉ እንዴት ለወደፊት ህይወታቸው ጠቃሚ የሆነውን የማንበብ ፍቅር ሊያዳብሩ ይችላሉ የሚለው ነው። ኢትዮጵያው ውስጥ የልጆች መፅሀፍት ብዙ የሉም። ይሄ አሜሪካና አውሮፓ ውስጥ የማይታሰብ ነው። ጎንደር ውስጥ ላይብረሪ ሰርተን መፅሀፎች ስንፈልግ አንድ አምስት መፅሀፍ ወዳአሳተመ የጀርመን ድርጅት ጠቆሙኝ። ያ ነው ምን ያክል የመፅሀፍ ችግር እንዳለ አሳየኝ።"
"ስለዚህ አላማችን ይህንን ክፍተት መሙላት ነው። አዳዲስ ታሪክ ያላቸው በኢትዮጵያ የተለያዩ ቋንቋዎች የተፃፉ 200 መፅሀፎችን ለማሳተም የሚጥር ሌላ ድርጅት እስካሁን አላውቅም። በሁለት ቋንቋዎች ስለሚፃፉ ልጆች የእንግሊዘኛ ችሎታቸውንም ያሻሽላሉ። ዋናው አላማችን ግን አንድ ላይብረሪ መሙላት የሚችል መፅሀፎችን ማዘጋጀት ነው።"
ድርጅታቸው ከተቋቋመ በአራት አመት ግዜ ውስጥ ኤልኖርና ሌይላ 105 ሺህ መፅሀፍትን በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚገኙ ህፃናት ያደረሱ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ 107ቱ በተለያዩ በጎ ፈቃደኞች የተፃፉ አዳዲስ ታሪኮች ናቸው። ሌይላም ከእናቷ ጋር በመሆን ሁለት መፅሀፎችን የፃፈች ሲሆን በተወለደችበት ሀገር ያሉ ህፃናትን መርዳት በመቻሏ በጣም ደስተኛ ናት።
"ልክ ማንም የማይወስድብኝ የተለየ ሀይል ያለኝ መስሎ እንዲሰማኝ ያደርገኛል። ለተወለድኩበት ሀገር የሆነ ነገር ማድረግ መቻሌ ለኔ በጣም ትልቅ ነገር ነው። አንድ ጊዜ የልጆች ትምህርት ቤት ሄጄ አንዲት ማንበብ የምትወድ ልጅ ተዋወኩ። በአማርኛም በእንግሊዘናም መፅሀፎቹን ስታነብ ሳያት በጣም ትልቅ ኩራት ተሰማኝ።"
መፅሀፎቹን ከመጻፏ በላይ ሌይላን የሚያስደስታት ግን እሷና እናቷ ኢትዮጵያ ውስጥ ትምህርት ማግኘት ላልቻሉና መፅሀፍትን እንደ ልብ ለማያገኙ ልጆች መፅሀፍት እንዲያገኙ መርዳታቸው ነው።
"ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ህፃናት እኔ ያነበብኳቸውን መፅሀፎች ማንበብ እንዲችሉ እፈልጋለው። እንደኔ የመጓዝ እንድል አግኝተው የተለያዩ ዓለሞችን እንዲያዩ፣ ያዩትንም ነገር እንዲፅፉ እመኛለሁ። "
ሌይላና እና እናቷ የሚያዘጋጇቸው መፅሀፎች በዋናነት ኢትዮጵያ ውስጥ ላሉ ህፃናት መማሪያ እንዲሆኑ የተዘጋጁ ቢሆኑም ድርጅቱ እራሱን በገንዘብ እንዲያግዝና የመግዛት አቅም ያላቸው ሰዎችም ቢሆኑ መፅሃፎቹን ለልጆቻቸው እንዲገዙ በአማዞን ድህረገፅ አማካኝነት ለገበያ ይቀርባሉ። መፅሀፎቹ ህፃናትን ማንበብና መፃፍን እንዲችሉ ከማገዝ በተጨማሪ ስነምግባርና ባህልንም የሚያሰርፁ ታሪኮችን እንዲይዙ ሆነው በበርካታ በጎ ፈቃደኛ ባለሙያዎች የተፃፉ እንደሆነ ኤልኖር ትገልፃለች።
"ይህን ድርጅት ያቋቋምነው በትብብር መስራት እንደምንችል በማመን ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሰራ ሌላ የእርዳታ ድርጅት መሆን አልፈለግንም። ስለዚህ አብረውን የሚሰሩ ብዙ አሉ። እንደውም አብረውን የሚሰሩ ሰዎች በጨመሩ ቁጥር ነው ስኬታችንን የመንለካው። ሁሉም ሰው እንዲሳተፍ እንፈልጋለን።"
"ለምሳሌ ዊማ የሚባል ድርጅት የኛን መፅሀፎች ወስዶ በጣም ገጠር በሆኑ የኢትዮጵያ ክፍሎች ወስጥ የሚገኙ ትምርህት ቤቶችና ላይብረሪዎች ያደርስልናል። ያ በጣም ያስደስተናል። ስለዚህ ሌሎች በኢትዮጵያም ከኢትዮጵያ ውጪም የሚገኙ አርቲስቶች፣ ፀሀፊዎች የዚህ ፕሮጀክት አካል እንዲሆኑ እንፈልጋለን።"
መፅሀፍትን ከማዳረስ በተቸማሪ ሌይላ እና እናቷ ሌይላ በተወለደችበት በባህር ዳርና ጎንደር ከተማ ላይብረሪ በመክፈት ለተማሪዎች አገልግሎት ይሰጣሉ።
ከእናቷ ጋር በምትሰራው በጎ ስራ ደስተኛ የሆነችው ሌይላ ስታድግ ፀሀፊ መሆን ትፈልጋለች።
"ሳድግ ፀሀፊ መሆን ነው የምፈልገው። ደስ የሚል ስራ ነው። በቃ ድንገት መፃፊያ አንስቼ ስፀፍ የራሴን አለም እፈጥራለሁ። ያን ማድረግ መቻሌ ልክ የተለየ ሀይል ያለኝ መስሎ እንዲሰማኝ ያደርገኛል።"
ሌይላና እናቷ ኤልኖር የሚወዱት አንድ የኢትዮጵያ አባባል አለ - ድር ቢያብር አንበሳ ያስር። ከተባበርን ኢትዮጵያ ውስጥ የተማሩ ህፃናትን ቁጥር ማሳደግ እንችላለን ብለው ያምናሉ። ከተለያዩ በጎ ፈቃደኞች ጋር በመተባበርም በዚህ አመት ብቻ ተጨማሪ 100 ሺህ መፃህፍትን ለኢትዮጵያ ህፃናት ለማዳረስ እቅድ አላቸው።