በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የኮቪድ-19 ክትባት


በዩናይትድ ስቴትስ የጃንሰን ኤንድ ጃንሰኑ የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት በተከታቢዎች ላይ ለአደጋ ሊዳርግ የሚችል የደም መርጋት ተከሰተ ያሉትን ሪፖርቶች ተከትሎ ክትባቱ መሰጠቱ በአስቸኳይ እንዲቆም የፌዴራሉ መንግሥት የጤና ባለሥልጣናት እያሳሰቡ ናቸው።

የዩናይትድ ስቴትስ የበሽታዎች መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ምዕከል /ሲዲሲ/ እና የምግብ እና የመድሃኒት አስተዳደር ዛሬ ማለዳ በጋራ ባወጡት መግለጫ ዕድሜያቸው ከአስራ ሦስት እስከ አርባ ስምንት በሆኑ ስድስት ሴቶች ላይ የተከሰተውን እጅግ ያልተለመደ ከባድ የደም መርጋት እየመረመሩ መሆናቸውን አስታውቀዋል። በተከታቢዎቹ ላይ የደም መርጋቱ የታየው በተከተቡ ከስድስት እስከ አስራ ሦስት ቀናቸው ውስጥ እንደሆነ ነው የተገለጸው።

የጃንሰን ኤንድ ጃንሰኑን የኮቪድ ክትባት ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ እስካሁን ከስድስት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን በላይ ሰዎች መከተባቸውን የጋራ መግለጫው ጠቅሷል።

በኒው ዮርክ ታይምስ ዘገባ መሰረት ከደም መርጋቱ በተያያዘ አንዲት ሴት ህይወታቸው አልፏል፤ ኔብራስካ ክፍለ ግዛት የሚኖሩ ሌላ ሴት ደግሞ በሆስፒታል በአስጊ ሁኔታ ላይ ናቸው።

ሲዲሲ የተከሰቱትን የደም መርጋት ችግሮች እና አጠቃላይ አንደምታውንም ለመገምገም በነገው ዕለት የክትባቶች አፈጻጸም ምክክር ኮሚቴውን ሰብስቦ እንደሚነጋገር አስታውቋል።

የኮቪድ-19 ክትባት ተያያዥ የደም መርጋት ጉዳይ ሲነሳ ይህ የጆንሰን ኤንድ ጆንሰኑ ክትባት ሁለተኛ መሆኑ ነው፤ ካሁን ቀደም በተመሳሳይ ሁኔታ በርካታ ሃገሮች የአስትራ ዜኒካ ክትባትን አስመልክተው አዳዲስ ደንቦች ማውጣታቸው ይታወሳል።

የአስትራ ዜኔካውን ክትባት በተመለከተ የአውሮፓ ህብረት የመድሃኒት ቁጥጥር ተቋም፣ ለህልፈት ሊዳርግ የሚችል የደም መርጋት፣ እጅግ በጣም ጥቂት በሆነ ቁጥር ሊከሰቱ ከሚችሉ የጎንዮሽ ጉዳቶች ዝርዝር ውስጥ ሊመዘገብ ይችላል።

ነገር ግን ክትባቱ የሚገኘው ጥቅም፤ ሊያደርስ ከሚችለው ጉዳት ጋር ሲነጻጸር እጅግ ከፍተኛ መሆኑን አስታውቀዋል።

XS
SM
MD
LG